የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣን ዘመናዊ የመንጃ ፈቃድ መታወቂያ መስጠት ጀመረ

አዲስ አበባ ጥር 3/2011 የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣን ከዛሬ ጀምሮ ዘመናዊ የመንጃ ፈቃድ ለአሽከርካሪዎች መስጠት መጀመሩን አስታወቀ።

የትራስፖርት ዘርፉን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያግዝ የአውቶሜሽን ሲስተም መዘርጋቱም ተጠቅሷል።

ዘመናዊውን የመንጃ ፈቃድ ለአሽከርካሪዎች ለመስጠት የሚያስችሉ 46 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው 14 ማሽኖች ለአገልግሎት መብቃታቸውን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ የመንጃ ፈቃዱ ቀደም ሲል ከመንጃ ፍቃድ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ ያነሳቸው የነበሩ ቅሬታዎችን የሚፈታ ከመሆኑም በላይ ሀሰተኛ መንጃ ፈቃድ ያስቀራል።

የኦሮሚያ ክልልን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማዘመን የተለያዩ የማሻሻያ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ባለፉት 7 ወራት ዘመናዊ የመንጃ ፈቃድ መታወቂያ ዝግጅት ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ባለስልጣኑ ስልጠናቸውን ጨርሰው መንጃ ፈቃድ ላልተሰጣቸው 60ሺ አሽከርካሪዎች በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ መንጃ ፈቃድ ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁንም ተናግረዋል።

አሽከርካሪው የያዘው መንጃ ፈቃድ ትክክለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ 3 ሺህ የማረጋገጫ መሳሪያዎች ለትራፊክ ፖሊሶች እንደሚከፋፈሉና ከዚህ በተጨማሪ 46 መፈተሻዎች በመጠቀም በየአቅጣጫው ቁጥጥር እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

አንዱ ማሽን ብቻ በቀን 1 ሺህ 2 መቶ የመንጃ ፍቃድ ማተም  እንደሚችልና ስልጠናውን ላጠናቀቁ አሽከርካሪዎች 600 ሺህ መንጃ ፈቃዶች መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።

በክልሉ ያለውን የትራስፖርት እንቅስቃሴ ዘመናዊ ለማድረግ የአውቶሜሽን ሲስተም መዘርጋቱን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸው፤ አንድ ተሸከርካሪ ከተገዛበት ቀን ጀምሮ መረጃዎችን በአንድ ማዕከል በመያዝ በኢንተርኔት አማካኝነት በየትኛውም ቦታ መረጃ ለማግኘት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ከማሰልጠኛ ተቋማት ጋር ተያይዞ ከዚህ በፊት ይሰጥ የነበረውን የፍቃድና እድሳት ስርዓትንም የማሻሻል ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የመንጃ ፍቃድ ማሰልጠኛዎች የንግድ ፈቃድ አሰጣጥ ወጥ እንዳልነበረ አስታውሰው ለነባርና አዲስ የመንጃ ፈቃድ ማሰልጠኛዎች ወጥ የሆነ የትምህርት ስርዓት መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

በአገሪቱ በስፋት እየደረሰ ያለው የትራፊክ አደጋ መንስኤዎች መካከል በሃሰተኛ የመንጃ ፈቃድ የሚያሽከረክሩ ግለሰቦች አንድ ምክንያት መሆናቸው ይታወቃል።

ከቅርብ አመታት ወዲህ እየተስፋፋ የመጣውን ሃሰተኛ የመንጃ ፈቃድ መታወቂያ ለመቆጣጠርና ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ የኦሮሚያ ክልል የወሰደው እርምጃ በአርያነት ይጠቀሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም