የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ መንግስትና ህብረተሰቡ በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ መንግስትና ህብረተሰቡ በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል
ጥር 3/2011 በሃገሪቱን የህግ የበላይነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ መንግስትና ህብረተሰቡ በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አስተያየታቸውን የሰጡ አንዳንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
በተለይ የታዳጊዎችን አመለካከት መቅረፅና የህግ ተገዢነታቸውን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው የቤት ስራ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አቶ ደመረ ተክሉ በሰጡት አስተያየት በሃገሪቱ የህግ የበላይነትን ለማሰፈን ጅምር ስራዎች ቢኖሩም “በወጥነት የህግ የበላይነት ተከብሯል ማለት አይቻልም” ብለዋል፡፡
ህዝብና መንግስት የየራሳቸውን ድርሻ ወስደው መስራት አለባቸው ያሉት አቶ ደመረ መንግስት የህግ የበላይትን በሚያስከብርበት ሰአት “ከጎኑ ሆነን መደገፍ አለብን ፤ብቻውን ያስከብራል ብዬ አላምንም” ብለዋል፡፡
የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ለሰላምና አንድነት መስራትን ከቃል ባለፈ በተግባር የምንደግፍበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ደርስናልም ነው ያሉት፡፡
ሃገሪቱን ወደ አልተፈለገ ክፍፍል ለማስገባት የሚሰሩ ሃይሎች አላማ እንዳይሳካ በህብረት መቆም እንደሚገባ የተናገሩት አቶ ደመረ የሃሰተኛ መረጃዎች ተቀባይ ባለመሆን ለሃገሪቱ ሰላም የድርሻቸውን ልወጡ እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡
የዜጎችን ተዘዋውሮ የመስራት ህገመንግስታዊ መብትን የሚያደናቅፉ አካላትን መንግስት እርምጃ ልወስድ ይገባል ያሉት አቶ ደመረ ወንጀለኞችን በማጋለጥ የሕብረተሰቡ ትብብር እንዲያድግ በየደረጃው መወያየት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ትምህርት ቤት ያሉ ታዳጊዎች የሃገር ተረካቢነታቸውን በሚመጥን ደረጃ መብትና ግዴታቸውን እንዲያውቁ መሰራት እንዳለበትም ነው የገለፁት፡፡
አቶ አለም ሰገድ አብረሃም በበኩላቸው በሃገሪቱ ሲካሄድ በነበረው በማንነት ፖለቲካ ምክንያት አሁን ላይ ዜጎች በፈለጉበት ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራትና ሃብት የማፍራት ሁኔታ አስቸጋሪ እየሆነ ነው ይላሉ፡፡
ዲሞክራሲ እየተገነባባት ባለች ሀገር የሃይል እርምጃን እንደ አማራጭ መውሰድ አይገባም ያሉት አቶ አለምሰገድ የህግ የበላይነት እንዳይከበር የሚሰሩ ሰዎችን በህግ ጥላ ስር እንዲቆዩ እና እንዲታረሙ መስራት የመንግስትና የሕብረተሰቡ ቀዳሚ የቤት ስራ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
“አንደኛ ችግር ፈጣሪዎች ማህበራዊ ሚዲያዎች ናቸው፣ እንደ ግል አቋም ባለፉት ሁለት ሶስት ወራት መጠቀምን አቁሜያለሁ’’ የምሉት አቶ አለምሰገድ፤ ማህበራዊ ሚዲያን ለጥሩ ነገር የመጠቀም ባህልን ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
ሃገሪቱ ሰላምና የተረጋጋች ሆና ኢኮኖሚውን መገንባት እንዲቻል የሊቢያና የሶሪያ እጣ ፋንታ እንዳይገጥመን በመነጋገር፣ በምክንያት በመተማመን የተሻለ መፍትሄ ማምጣት ይገባል ብለዋል፡፡
በተለይ አብዛኛው ወጣት የሥራ እድል ተጠቃሚ ባለመሆኑ አሁን የሚታየው ችግር ተፈጥሯል ያሉት አቶ አንዱ አለም “ወጣቱን አደራጅተን ስራ አሲዘናል” ለሚለው ምን ያህሉ ህይወታቸው ተቀየረ በማለት ማጤን ይገባልም ብለዋል፡፡
የሕግ የበላይነትን በሀገራችን ለማስፈን አመራሮች አርአያ መሆን እንዳለባቸው ገልጸው ሰውን በሰውነቱ እንጂ በማንነቱ ባለመፈረጅ፤ አመራር ሰጪነትን በብቃት መነፅር በመመልከት ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ አብሮ የመኖር ችግር የለበትም ያሉት አቶ አንዱአለም የፖለቲካ አመራሮች በሃገሪቱ ለሚፈጠረው ችግር ኃላፊነት ወስደው ሊሰሩ ይገባልም ብለዋል፡፡
“ጥሩ ነገር አየን ደግሞም እናያለን” በምንልበት ሰአት በሃገሪቱ የተለያዩ አካበቢዎች ሰላም መጥፋት ያሳዝነናል ያሉት ወይዘሮ ተዋበች ሹራ “በአሁኑ ሰአት ችግሮች በጠረጴዛ ዙሪያ ነው ሊፈቱ የሚገባው እንጂ አፈ ሙዝ እንደ አማራጭ አይታይም” ብለዋል፡፡
ሰላም ከቤት እንደሚጀምር የተናገሩት ወይዘሮ ተዋበች ልጆች ሲያጠፉ ጥፋታቸው እየተነገራቸው እንዳይደግሙት እንደሚቀጡ ሁሉ ሀገሪቷን ሰላም በመንሳት ችግር እየፈጠሩ ባሉት አካላት ላይ አስተማሪ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል ፡፡
ትምህርት ቤቶች፣ እድሮችና በቤተ እምነቶች በተለይ አንድነትና ሰላም ላይ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ የሚገልጸው ወጣት ዳዊት ሳንቃ የመንግስት ህግ አውጪው፣ አስፈፃሚና ተርጓሚው የህዝቡን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ተቀናጅተው ሊሰሩ ይገባል ብሏል፡፡
የህግ ተገዢነት ከቤተሰብና ከአካባቢ ይጀምራል የሚለው ዳዊት፤ ልጆች ሲያጠፉ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን የአከባቢም ሰው ገፅፆ የሚመልሳቸው ሁኔታ እየቀረ መምጣቱ አሉታዊ ተፅእኖ እንዳለው ነው የተናገረው፡፡
’’ለውጥ የሚመጣው ቀስ በቀስ ነው፣ ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ሰው ሌላውን እንደራሱ መውደድ ይገባዋል፤ ምን ቸገረኝነትና ምን አገባኝ የለውጥ እንቅፋች ናቸው” ብሏል፡፡
ለለውጡ የሰዎች መነሳሳት ወሳኝ መሆኑን የተናገረው ወጣቱ ፤ ለውጡን ለማስቀጠልም አመራሩ በፈጠራ ላይ ማተኮር፣ ማስፋፋት እንዲሁም በእውቀት መምራት ያስፈልጋል ብሏል፡፡