በዓሳና ሌሎች ብዝሃ ህይወት ሀብቶች ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዓሳና ሌሎች ብዝሃ ህይወት ሀብቶች ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ እየተካሄደ ነው
ሀዋሳ ጥር 3/2011 በዓሳና ሌሎች የውሃ ብዝሃ ህይወት ሀብቶች ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አቶ አያኖ በራሶ እንደገለጹት ዓሳን ጨምሮ በውሃ ውስጥ ያሉ ብዝሃ ሕይወትን በመጠቀም ረገድ እንደ አገር ያለውን ውስንነት መፍታት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድርሻ ነው፡፡
ዘርፉ በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ የምጣኔ ሀብት ምንጭ እንደሚሆንና በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ ባለፈ ሥራ እንደሚፈጥርም አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓሳ ምርት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘቷ በጥናት መረጋገጡን አቶ አያኖ ተናግረዋል፡፡
ህንድ በዓሳ ላይ ብቻ ምርምር የሚያደርግ ዩኒቨርሲቲ መክፈቷን ለአብነት የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ በመድረኩ ላይ በዘርፉ ልምድ ካላቸው ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ተመራማሪዎች የሚያቀርቡት ጥናት ልምድ የሚወሰድበት ነው፡፡
በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮና ኮምፒቴሽናል ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ዘይቱ ጋሻው በበኩላቸው በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሚገነቡ ግድቦች ለዓሳ ርባታ ተጨማሪ አቅም የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡
በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት ዓሳን እንደ አንድ የምግብ አማራጭ መጠቀምና የሀብት ምንጭ ለማድረግ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ የዓሳ ሳይንስን የሚያጠኑ ምሁራን ማፍራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በዓሳ ሳይንስ ላይ ትኩረት በማድረግ በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ተማሪዎችን እያስተማረ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ዘይቱ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በዶክትሬት ዲግሪ መርሐ ግብር ስልጠና ለመስጠት የሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው እያስገነባ ባለው ሰው ሰራሽ ኩሬ አማካይነት የዓሳ ጫጩቶችን በማራባት ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት እንደሚጀምር ጠቁመዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ዙፋን በደዊ ኮንፍረንሱ ዓሳን ጨምሮ በውሃ ውስጥ ባሉ ብዝሃ ህይወት ላይ ዓለም የደረሰበትን ለማወቅ ያስችላል። እንደ አገር የሚታዩ ክፍተቶችን ለማወቅም ያስችላል፡፡
ለሶስት ቀናት በሚቆየው ኮንፍረንስ ከአውሮፓ፣አሜሪካ፣ እስያና አፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 42 ተመራማሪዎች እየተሳተፉ ነው።60 የሚሆኑ ጥናታዊ ጽሁፎች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡