ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከዲፕሎማቶችና ሚሲዮኖች ጋር ሊወያዩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከዲፕሎማቶችና ሚሲዮኖች ጋር ሊወያዩ ነው
አ
አዲስ አበባ ጥር 3/2011 ኢትዮጵያ ከዓለም ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጎልበት በተለያዩ አገራት የሚገኙ ዲፕሎማቶችና ሚሲዮኖች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ውይይት እንደሚያደርጉ ተገለጸ።
ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ወራት ያከናወነችው ዲፕሎማሲያዊ ስራ የአገሪቱን ጥቅም በማስጠበቅና ኢትዮጵያዊነትን ለዓለም አጉልቶ በማሳየት ፍሬያማ እንደነበር ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ የነበሩት አቶ መለስ ዓለም ለአዲሱ ተተኪያቸው አቶ ነቢያት ጌታቸው ኃላፊነታቸውን ባስረከቡበት ወቅት በሰጡት መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በመጪው ሰኞ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች እና በተለያዩ አገራት ከሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖችና ዲፕሎማቶች ጋር ይወያያሉ።
በውይይቱ ነባርና አዳዲስ ተሿሚዎችን ጨምሮ ከ60 በላይ አምባሳደሮች የሚሳተፉ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መዋቅራዊ ለውጥና የአገሪቱ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ውይይት ይደረግበታል።
ኢትዮጵያ ታላቅነቷን በዓለም አደባባይ እንድታስመሰክር ዲፕሎማቶችና አምባሳደሮች ማድረግ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ በሰፊው እንደሚመክሩ ገልጸዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር የአንድ ቀን ውይይት ከተደረገ በኋላ በዝርዝር የስራ ዘርፎች ላይ የተናጠል ግምገማ ይደረጋል ነው ያሉት።
በተጨማሪም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር በወቅታዊ አገራዊ፣ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የፓናል ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ወራት 10 የተለያዩ አገራት መሪዎች ማስተናገዷን የገለጹት አቶ መለስ፤ "ይህ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ የመሆኗ ማሳያ ነው" ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ኃላፊነታቸውን ለተተኪው አቶ ነብያት ጌታቸው አስረክበዋል።
አዲሱ ቃል-አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰሜንና ደቡብ አሜሪካና ካሪቢያን ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና የጽህፈት ቤቱ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ዳይሬክተር፣ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ የኮሙኒኬሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተር ሆነውም አገልግለዋል።
በካናዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር አማካሪ፤ በሲዊድንና በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማትም ነበሩ።
አቶ ነቢያት ጌታቸው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንግሊዝ ከሚገኘው ሊድስ ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ኮሙኒኬሽን አግኝተዋል።
ላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር እንደሚወያዩ ተገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኬንያ አምባሳደር ተደርገው በተሾሙት የሚኒስቴሩ የቀድሞ ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ቦታ አቶ ነብያት ጌታቸውን ተክቷል።
ሚኒስቴሩ ዛሬ በሰጠው ሳምንታዊ የወቅታዊ ጉዳዮች መግለጫ ላይ እንዳመለከተው፤ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮችና አምባሳደሮች የአገሪቱ ቀጣይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሚዳብርበት ሁኔታ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ይወያያሉ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማሻሻያ፣ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ያከናወነችው ተግባራትና የቀጣይ ዲፕሎማሲያዊ አቅጣጫ ላይ ውይይት ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ታውቋል።