ቀጥታ፡

በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ሳቢያ በኢንዱስትሪዎች ላይ ለሚደርስ ከፍተኛ ጉዳት ካሳ ለመክፈል የሚያስችል ዋስትና ሊገባ ነው

አዲስ አበባ ጥር 2/2011 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኤሌክትሪክ መቆራረጥ በከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞቹ ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ካሳ ለመክፈል የሚያስችል ዋስትና ለመግባት ተዘጋጅቻለሁ አለ።

ተቋሙ ከከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞቹ ጋር በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በዛሬው እለት ውይይት አካሂዷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በዚሁ ወቅት እንዳሉት በተደጋጋሚ በሚገጥማቸው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በኢንዱስትሪ መሳሪያዎቻቸው ላይ ጥፋት እየደረሰ ነው።

ስለዚህም ተቋሙ በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ለሚደርሰው ጉዳት መፍትሄ መስጠት እንዳለበት ነው የገለፁት።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ተወካይ አቶ ጌታቸው ትኩዬ እንዳሉት በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በገጠመ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ሳቢያ በርካታ የመቆጣጠሪያ ካሜራዎችና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ተቃጥለዋል።

ይህም በዘርፉ አድገትና ባለሃብቶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ ለሚደርሱ ጉዳቶች የሚሰጥ ዋስትና ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሀበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ አዳነ፤ የኢትዮጵያ ጂቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ተወካይ አቶ ደምሱ ለገሰም በተመሳሳይ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ በኢንዱስትሪዎች ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት ዋስትና ሊሰጥ ይገባል ነው ያሉት።  

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አብርሃም በላይ በሰጡት ምላሽ ተቋሙ ከኤሌክትሪክ መቆራረጥ ጋር በተያያዘ ለሚከሰት ጉዳት ዋስትና ለመግባት ድርጅታቸው መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

በዚህም መሰረት ደንበኞች ለሚደርስባቸው ጉዳት አስፈላጊውን ማካካሻ ይሰጣል፤ ከዚህ በፊት ለደረሱ ጉዳቶች ደግሞ አገልግሎቱን ሲሰጥ ከነበረው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመነጋገር መፍትሄ ይዘይዳል ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የአገልግሎት ክፍያን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ውዝፍ ክፍያ ይከፍሉ እንደነበር ጠቅሰው ይህ ችግር አሁን በዚህ ተቋም ሊኖር አይገባም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልም ደንበኞቹ በየወሩ የአገልግሎት ክፍያን በመሰብሰብ ይህ አይነት ችግር እንዳይፈፀም እንደሚሰራ ነው የገለፀው።

ከ66 ኪሎ ቮልት በላይ የኤክትሪክ ተጠቃሚዎች ከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚዎች ውስጥ የሚመደቡ ናቸው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም