የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደገና ሊቋቋም ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደገና ሊቋቋም ነው
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ብቁና ተወዳዳሪ ሆኖ የተጣለበትን አገራዊ ተልእኮ በአግባቡ መወጣት እንዲችል እንደገና ሊቋቋም ነው።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ኢዜአን እንደገና ለማቋቋም በቀረበለት ረቂቅ አዋጅ ላይ መክሯል።
በረቂቅ አዋጁ መግለጫ ላይ እንደተመለከተው ኢዜአ ተልእኮውን ለመወጣት በሚያደርገው ጥረት እንደአገራዊ የዜና ተቋምነቱ ሥራውን ማስፋፋትና አቅሙን እያሳደገ መሄድ እንዲችል ለማድረግ ነው እንደገና እንዲቋቋም የተፈለገው።
ኢዜአ ከሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች በተለየ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሄራዊ መግባባት እንዲፈጠር የሚያግዙ ዜናና ዜና ነክ ዘገባዎችን በስፋት መስራትና ለአገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሃን ማድረስ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተጠቀሱት የኢዜአ ስልጣን መካከል ይገኝበታል።
ኢዜአ እንደገና መቋቋሙ በዋና ዋና አገራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ለሚደረገው ትግል የበኩሉን ሚና ከመወጣት ባለፈ የአገሪቱን መልካም ገፅታ የመገንባት ተልዕኮውንም በአግባቡ እንዲወጣ እንደሚያግዘው መግለጫ ያትታል።
በአዲሱ አዋጅ መሰረት ኢዜአ የራሱን አቅም ማሳደግና በገንዘብ መደጎም፤ ብሎም ተወዳዳሮ መሆን ይችል ዘንድ ገቢ በሚያስገኙ ሥራዎች መሰማራት ይችላል።
ይህም የተሻለ ሙያዊ አቅም ያላቸውን ባለሙያዎች ከገበያው ተወዳድሮ ለማግኘትና ይዞ ለማቆየት እንዲሁም ምቹ የሥራ አካባቢ ለመፍጠር እንደሚያስችለው ተገልጿል።
ምክር ቤቱ ኢዜአን እንደገና ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከመከረ በኋላ ለተጨማሪ እይታ ለህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ላለፉት 75 ዓመታት በተለያዩ አደረጃጀቶች እየተዋቀረ የአገሪቱ ዋነኛ የዜና ምንጭ በመሆን ሲሰራ ቆይቷል።
ተቋሙ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ባሉት 38 ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ወኪሎችን መድቦ ዜናና ዜና ነክ መረጃዎችን በመዘገብ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ያሰራጫል።