ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አሰራሩን ሙሉ ለሙሉ ወደ ዲጅታል ሊቀይር ነው

146

አዲስ አበባ ጥር 2/2011 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከ3 እስከ 5 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ አሰራሩን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጅታል ለመቀየር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ማህበሩ በአዲስ መልክ ያደራጀውን ድረ-ገጽም ዛሬ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስመርቋል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የስትራቴጂና ፈጠራ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ዳግማዊት አማረ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ማህበሩ አሰራሩን ሙሉ ለሙሉ ከወረቀት ነጻ በማድረግ ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየሰራ ነው።

ውድድሮች በሚዘጋጁበት ወቅት ከተሳታፊዎች ጋር የሚደረገው ግንኙነት ብዙ ጊዜና ገንዘብ እንደሚወስድ የጠቆሙት ስራ አስኪያጇ ድረ ገጹን በአዲስ መልክ ማደራጀት አሰራሩን ዲጂታል የማድረግ ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

ከውድድር ተሳታፊዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ይነሳ የነበረው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከውድድር ተሳታፊዎችና ባለድርሻዎች ጋር ያለውን ግንኙነት የተቀላጠፈ፣ፈጣንና ተደራሽ ማድረግ እንደነበርም አንስተዋል።

በመሆኑም በተቀረፀው ስትራቴጂ መሰረት ከሶስት እስከ አምስት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ውድድር ማዘጋጀት ስራውን ወደ ዲጂታል ያዘምናል ብለዋል።

እንደ ወይዘሮ ዳግማዊት ገለፃ አሁን በአዲስ መልክ የተደራጀው ድረ- ገፅም የውድድር ተሳታፊዎች መረጃዎችን በቀላሉ አግኝተው ከታላቁ ሩጫ ጋር ቀጥታ መገናኘት ከማስቻሉም ባለፈ የሶስተኛ ወገን የመረጃ ስርጭትን ያስቀራል።

በ2012 ዓ.ም በሚካሄደው 19ኛው ውድድር ተሳታፊዎች ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ አስር ቀናት ድረ ገፁ ላይ በመግባት ቦታ መያዝ (Online Reservation) ማድረግ የሚቻል መሆኑን ጠቁመዋል።

ኦንላይን የምዝገባ ክፍያውን ለመጀመር ደግሞ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመነጋገር የክፍያ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ውይይት ይደረጋል ብለዋል።

የተሳታፊዎችን የመረጃ ቋት ወደ ኤሌክትሮኒክስ የመቀየር ተግባርም እንደሚከናወን ወይዘሮ ዳግማዊት ተናግረዋል።

ድረ ገጹን የሰሩት የእንግሊዙ "ዲጂታል ቲክል" ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ዴቪድ ሲዌል በበኩላቸው ድረ-ገጹ "ፕሮግረሲቭ ዌብ አፕ" እና "ፋይር ቤዝ" የሚባሉ ቴክኖሎጂዎችን ይጠቀማል ብለዋል።

ቴክኖሎጂው በጎግል ኩባንያ ስር በመሆኑ ለአደጋ ያለው ተጋላጭነት አነስተኛ እንደሆነ ጠቅሰው ድረ ገጹን በፍጥነት ለመክፈትና በቀላሉ ለመጠቀም እንደሚያስችልም አስረድተዋል።

በቀጣይ በድረ ገጹ ላይ ተወዳዳሪዎች የሚወዳደሩበትን ቦታ የሚያሳይ ካርታ፣በሞባይላቸው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስለ ውድድሮች የሚተላለፉ መልዕክቶችን እንዲያገኙና ውድድሮችን በቀጥታ የሚከታተሉበት አሰራር ይካተትበታል ብለዋል።

በተጨማሪም ተወዳዳሪዎች በሞባይላቸውን መረጃ ከድረ ገጹ ጋር በማገናኘት የገቡበትን ሰአት እንዲያውቁ እንደሚደረግም አስረድተዋል። 

በዚህም መሰረት ተገልጋዮች በድረ ገፁ www.ethiopianrun.org መጠቀም ይችላሉ ተብሏል። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከተመሰረተበት ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን 137 ውድድሮችን አካሂዷል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም