በአገሪቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ስርዓት እውን እንዲሆን ኃላፊነታችንን እንወጣለን- የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
በአገሪቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ስርዓት እውን እንዲሆን ኃላፊነታችንን እንወጣለን- የፖለቲካ ፓርቲዎች
አዲስ አበባ ጥር 2/2011 በኢትዮጵያ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ስርዓት እንዲፈጠር የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግና ደንቦች፣ የምርጫ ስርዓት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ 573/2000 እና የምርጫ አለመግባባቶች አፈታት ላይ ፓርቲዎች እየተነጋገሩ ነው።
የውይይቱ ተሳታፊ ከሆኑት ፓርቲዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው በሰጡት አስተያየተ እንዳሉት በአገሪቱ የሚካሄዱ ምርጫዎች ሰላማዊ፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ከፍተኛ ነው።
ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ለራስ ጥቅምና ፍላጎት ሳይሆን ቅድሚያ ለአገርና ለህዝብ ሰላም መስራት አለበት ሲሉም ነው የተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ተወካዮች የገለፁት።
ይህ ሲሆን ነው ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ የምርጫ ስርዓትን በአገሪቱ መተግበር የሚቻለው ሲሉም አመልክተዋል።
ከአርጎባ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የተወከሉት አቶ መሃመድ ሙሳ አበጋዝ "የምርጫ ስርአቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የግል ፍላጎትን ወደጎን በመተው ለአገሪቱ ሰላም በመቆርቆር መስራት ያስፈልጋል" ብለዋል።
አክለውም "በአገሪቱ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ ከስልጣን ይልቅ ቅድሚያ አገርን፣ ህዝብንና ሰላምን በማስቀደም በጋራ መስራት ግድ ይላል" ነው ያሉት።
የመላ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ኑሪ ሙደሲር በበኩላቸው ፓርቲዎች ከምርጫ ቅስቀሳ ጀምሮ እስከመጨረሻው ውጤት ድረስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሰላማዊና ገንቢ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።
ሁሉም ዜጋ በሰላምና በነጻነት ወጥቶ መምረጥ እንዲችል ከወጣቶች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ከምሁራን ጋር በጋራ በመሆን እንደሚሰሩ የገለጹት ደግሞ ከሲዳማ አርነት ንቅናቄ የተወከሉት አቶ ለገሰ ላሉቃሞ ናቸው።
በዚህም ሁሉም ፖለቲካ ፓርቲ ለአገሩ ተቆርቋሪ በመሆንና ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት በሃላፊነት ስሜት በጋራ መስራት እንደሚገባቸው ነው የገለጹት።
ካለፉት በርካታ ዓመታት ጀምሮ ሥራ ላይ የሚገኘው የአገሪቱ የምርጫ ህግና አሰራር 'ለዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ምርጫ የሚመች አይደለም' የሚል ቅሬታ በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይቀርባል።
ካለፉት ጥቂት ወራት ጀምሮ ግን የኢትዮጵያ የምርጫ ስርዓት ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ገለልተኛ ይሆን ዘንድ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድን እንደገና ማቋቋምን ጨምሮ መንግስት የተለያዩ የማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ነው።
ይህም ፓርቲዎች በአገሪቱ በሚካሄዱ የምርጫ ፉክክሮች ላይ በኃላፊነትና በነጻነት እንዲሳተፉ፤ ዜጎችም የሚሹትን እንዲመርጡ ያስችላቸዋል የሚል እምነት ተጥሎበታል።