ስምንተኛው የከተሞች ፎረም በጂግጂጋ ከተማ ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
ስምንተኛው የከተሞች ፎረም በጂግጂጋ ከተማ ይከበራል
አዳማ ጥር 2/2011 ስምንተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በሶማሌ ክልል ጂግጂጋ ከተማ እንደሚከበር የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴሩ የመልካም አስተዳደርና አቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ተሾመ እንደገለጹት ፎረሙ "መደመር ለኢትዮጵያ ከተሞች ብልጽግና" በሚል ከየካቲት 9/2011ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ቀናት ይካሄዳል፡፡
ፎረሙን በማስመልከት ዛሬ በአዳማ ከተማ ለመገናኛ ብዙሃን ፣ለጦማሪያንና ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
የክልሉ መንግስትም ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብም የከተማዋን ልማት የማጠናከርና የመስተንግዶ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዜር ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው ለፎረሙ ስኬታማነት የመገናኛ ብዙሃንና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በፎረሙ 200 ከተሞች የሚሳተፉ ሲሆን ይህም ከተሞች ለጋራ እድገት የልምድ ልውውጥ በማድረግና በመካከላቸውን ጤናማ የውድድር መንፈስን በማጎልበት ልማታቸውን ለማፋጠን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሏል፡፡