ፌዴሬሽኑ በድሬድዋ ከተማው ተጫዋች ኢታሙኒ ኮሙኒ እና በወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ ላይ የቅጣት ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ ጥር 2/2011 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፒሊን ኮሚቴ በድሬድዋ ከነማው ተጫዋች ኢታሙኒ ኮሙኒ እና  በወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ ላይ የቅጣት ውሳኔ አሳለፈ።

ኮሚቴው የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው በኢትዮጵያ ፕሪሚሪሊግ 9ኛ ሳምንት ጨዋታ ታህሳስ 21 ቀን 2011 ዓ.ም ወላይታ ድቻ ከድሬድዋ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ የተከሰተውን የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ተከትሎ ነው።

በእለቱ  ጨዋታ የድሬድዋው ተጫዋች ኢታሙኒ ኮሙኒ የወላይታ ዲቻውን ተጫዋች ሙባረክ ሽኩር በቦክስ በመማታቱ ከ500 በላይ የወላይታ ዲቻ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ በመግባት ችግር እንዲከሰት አድርጓል።

ተጨዋቹ በእለቱ ለተከሰተው የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያት በመሆኑ ኮሚቴው በ8 ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ እንደይሰለፍ እንዲሁም 15 ሺህ ብር ቅጣት እንዲከፍል ተወስኖበታል።

ተጨዋቹ እንዲከፍል የተወሰነበትን ብር በቀጣዮቹ ሰባት ቀናት ውስጥ ለፌዴሬሽኑ ገቢ እንዲያደርግ የተባለ ሲሆን ከተባሉት ቀናት ሳይከፍል ካለፈ ግን በየቀኑ የሁለት በመቶ ጭማሪ እንዲከፍል ይደረጋል ተበሏል።

ክፍያውን በተባለው ጊዜ ካልፈፀመ ከፌደሬሽኑ ምንም አይነት አገልግሎት እንደማያገኝም ተገልጿል።

ናሚቢያውዩ ተጨዋች ኢታሙና ኮሙኒ ድሬድዋ ከተማን የተቀላቀለው በ2011 ዓ.ም ሲሆን እስካሁንም ለክለቡ አራት ጎሎችን አስቆጥሯል።

በተመሳሰይ የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች በእለቱ የድሬድዋን እግር ኳስ ቡድን መጓጓዣ ሰርቪስ መስታወት በመስበራቸው እንዲሁም የመኪናው ሾፌር ላይ ጉዳት በማድረሳቸው ክለቡ ቅጣት ተላልፎበታል።

በመሆኑም የወላይታ ድቻ እግር ኳስ ክለብ ሾፌሩ ለህክምና ያወጣውን ሙሉ ወጪ እንዲሁም የተሰበረውን የመኪና መስታወት ወጪ እንዲሸፍን መወሰኑን ኮሚቴው አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም