ቀጥታ፡

የመዲናዋ የስፖርት ለሁሉም ውድድር ጥር 4 ይጀምራል

አዲስ አበባ ጥር 1/2011 በዘንድሮ በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ለሁሉም ኮሚቴ የሚከናወነው 9ኛው የስፖርት ለሁሉም ውድድር ከጥር 4 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ይካሄዳሉ።

የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ ድርጅቶችና የጤና ቡድኖች ልዩ ልዩ የስፖርት ውድድርና 8ኛው የሚዲያና የኪነጥበባት ባለሙያዎች የእግር ኳስ ውድድር አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

9ኛው የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ ድርጅቶችና የጤና ቡድኖች ልዩ ልዩ የስፖርት ውድድሮች በእግር ኳስ ወንዶች እንዲሁም በመረብ ኳስ፣ በጠረጴዛ ቴኒስ፣ አትሌቲክስ፣ ገመድ ጉተታ፣ ቼስ፣ ቢሊያርዶ(ፑልና ከረንቡላ)፣ ዳማና ዳርት በሁለቱም ጾታዎች 2ሺህ725 ተሳታፊዎች ይኖራሉ።

በውድድሩ ላይ በመዲናዋ የሚገኙ የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆችና ትምህርት ቤቶች ይሳተፋሉ።

8ኛው የሚዲያና የኪነጥበባት ባለሙያዎች የእግር ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲን ጨምሮ 10 የሚዲያ ተቋማት አንድ የአርቲስቶችና አንድ የዲጄዎች ቡድን በድምሩ 12 ቡድኖች እንደሚሳተፉ ታውቋል።

ሁለቱም ውድድሮች ጥር 4 ቀን 2011 ዓ.ም በእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በሚካሄዱ የመክፈቻ ጨዋታዎች ይጀመራሉ።

የስፖርት ለሁሉም ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አቶ ዘነበ ተሰማ እንደገለጹት፤ የውድድሮቹ አላማ ሰራተኛውን በስፖርት ለሁሉም ፕሮግራም በማሳተፍ ጤናው እንዲጠበቅና አምራች ዜጋ እንዲሆን ማስቻል ነው።

ህብረተሰቡ ማህበራዊ ግንኙነቱ ማጠናከርና የልምድና የስራ ባህል ለውጥ እንዲያደርግ ከማድረግ አንጻር የውድድሮቹ መካሄድ ያለው ሚና ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል።

የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ድርጅቶችና የጤና ቡድኖች ልዩ ልዩ የስፖርት ውድድሮች በ2000 ዓ.ም ሲጀመር ከ20 በታች የነበረው የተሳታፊ ቡድኖች ብዛት በአሁኑ ውድድር ላይ 66 መድረሱን ጠቅሰዋል።

በሚዲያና የኪነጥበባት ባለሙያዎች የእግር ኳስ ውድድር ላይም የተሳታፊዎች ቁጥር ከስድስት የማይበልጡ እንደነበርም አውስተዋል።

ውድድሮቹ ከተጀመሩበት ጊዜ አንስተው በቡድኖች መካከል ያለው ቤተሰባዊ ትስስር እየዳበረ በመምጣቱ አጥጋቢ ውጤት እንደተገኘም ነው አቶ ዘነበ ያስረዱት።

ቡድኖች ከመስከረም 2011 ዓ.ም ጀምሮ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑንና የውድድሮቹ ቀን የተራዘመ እንዲሆን የተደረገው ዓመቱን ሙሉ ሰራተኞቹ በስፖርት እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲቆዩ ለማድረግ ታስቦ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የስፖርት ለሁሉም ኮሚቴ የጽህፈት ቤት ሃላፊ ፈቃደ ጫካ በበኩላቸው በውድድሮቹ መክፈቻ ቀን ተሳታፊዎች ከ15 እስከ 20 ደቂቃ የሚቆይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በሚዲያና የኪነጥበባት ባለሙያዎች ውድድር አዲስ አበባ ካሉ መገናኛ ብዙሃን በተጨማሪ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ እንደሚሳተፍ ጠቁመዋል።

ከሁለቱ ውድድሮች በተጨማሪ በተያዘው በጀት ዓመት ከተማ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ፌስቲቫል፣ የስፖርት ለሁሉም ሳምንት፣ 2ኛው የሚዲያ የፉትሳል ውድድርና የኦሎምፒክ ቀን ማክበር በስፖርት ለሁሉም ፕሮግራም ውስጥ ያሉ ሁነቶች እንደሆኑ ተናግረዋል።

ውድድሮቹና ፌስቲቫሎቹ የሚካሄዱት ''ሁሉም ህብረተሰብ በሚኖርበት በሚሰራበትና በሚማርበት አካባቢ ስፖርትን ተደራሽ ማድረግ'' በሚል በስፖርት ፖሊሲ ላይ ከተጠቀመጠው ግብ ጋር የተዛመደ እንደሆነም አስረድተዋል።

አጠቃላይ ለውድድሩ በቂ ዝግጅት መደረጉንም አቶ ፈቃደ ጠቁመዋል።

ውድድሩ በስፖርት ለሁሉም ኮሚቴ የሚመራ መሆኑንና ንዑሳን ኮሚቴዎችም ተቋቁመው ውድድሮችን እንደሚከታተሉ በመግለጫው ወቅት ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም