ቀጥታ፡

ፓርቲዎች በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት ደጋፊዎቻቸውንና አባላቶቻቸውን በማሰማራት እየሰሩ ነው

አዲስ አበባ ጥር 1/2011 በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ ግጭቶችን ለመፍታት ደጋፊዎቻቸውና አባሎቻቸውን በየአካባቢው በማሰማራት እየሰሩ መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ።

በአገሪቷ ነጻ፣ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ  በሰላም ጉዳይ በጋራ መስራት ቀዳሚ ተግባር መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን ለውጥ ተከትሎ ለረጅም ዓመታት በውጭ ሲታገሉ የነበሩ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ በፖለቲካ ለመሳተፍ ወደ አገር መግባታቸው ይታወሳል።

በቅርቡ ወደ አገር ቤት ከገቡ ፓርቲዎች መካከል ደግሞ የኦሮሚያ ብሄራዊ ፓርቲና የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ግንባር ይገኙበታል።

እነዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በተለያዩ የውጭ አገሮች ሲያደርጉ የነበረውን የትጥቅ ትግል ትተው በሰላማዊ መንገድ ለመሳተፍ ወደ አገራቸው መግባታቸውን የፓርቲዎቹ ሃላፊዎች ይናገራሉ።

ይሁንና በአሁን ጊዜ በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ ግጭቶች ከዓላማቸው እንደሚያደናቅፋቸውም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ግጭቶቹን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እንደ ፓርቲ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት እየሰሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

የሚታየው ሰው ሰራሽ ግጭት እንዲፈታና የመፍትሄ አካል ለመሆን ያላቸውን የሰው ሃይል እንደሚጠቀሙ ገልጸው የህዝቡን ግንዛቤ ለማሳደግና አንድነትን ለማምጣት የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወኑ መሆኑን  ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ግንባር የሰላም አደራዳሪ ቡድን ሃላፊና የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጌታነህ ዘለቀ እንዳሉት  በየቦታው የሚደረገው ግጭት ሰው ሰራሽ ለመፍታት አባሎቻችንንና ደጋፊዎቻችንን በማሰማራት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት  እየሰራን ነው ብለዋል፡፡ 

የኦሮሚያ ብሄራዊ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሊበን ዋቆ በበኩላቸው  ''ይሄ ለውጥ ግቡን የሚመታው ህዝቡ ዕውቀት ሲኖረው አንድነት ሲኖረው ለብሄራዊና ለህብረተሰባዊ ጥቅሙ የሚንቀሳቀስበት ብቃት ሲኖረው ነው።ይሄንን ለማሟላት በተቻለ መጠን ጥረት እያደረግን ነው”

በሌላ በኩል በአገር ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሰላምን ቀዳሚ የቤት ስራቸው በመሆኑ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት እየሰሩ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

ህዝብ ከህዝብ ጋር ተግባብቶና ተከባብሮ የሚኖርበትን ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት የሚያደርጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

''ህዝብ እንዲረጋጋ ህዝብ ከሌላው ወንድም ህዝቡ ጋር ከመጋጨት ይልቅ ተግባብቶ አብሮ የሚኖርበት ተከባብሮ ሰላም ፈጥሩ አብሮ የሚኖርበት ዕድል እንዲኖር ነው ጥረት እያደረግን ያለነው።'' ያለው የአረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ ነው፡፡

''ጋህአዴን አሁን ወደ ክልሉ እየገቡ ያሉ ፓርቲዎች አሉ በቅርቡ የተመዘገቡ ከውጭ አገርም የገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ። ስለዚህ እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ጋምቤላን ሰላም ማድረግ ለቀጣይ ምርጫ ዝግጁ የማድረግ ስራ በጋራ እየሰራን ነው ያለነው።''የሚሉት የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አባል ቶክ ቾት ናቸው፡፤

በኢትዮጵያ በመጣው ለውጥ በተለያየ መንገድ ትግል ያደርጉ የነበሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደአገር ገብተው በሃሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ትግል ማድረግ መጀመራቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም