ቀጥታ፡

የጉጂ ኦሮሞ አባ ገዳዎች የሰላም ጥሪ አቀረቡ

ነገሌ ጥር 1/2011 የጉጂ ኦሮሞ አባገዳዎች   አለመግባባቶች በድርድር እንዲፈቱ ፣ የህግ የበላይነት እንዲከበርና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ አቀረቡ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ ጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም. በነገሌ ከተማ በባህላዊ የገዳ ስርዓት የሰላም ሳምንት እንደሚታወጅ አባ ገዳ ጂሎ ማኖ አስታውቀዋል፡፡

የሰላም ሳምንትን አስመልክቶ ከአዶላና ሻኪሶ ወረዳዎች የሀገር ሽማግሌዎችና ከኃይማኖት አባቶች እንዲሁም ከሌሎች ነዋሪዎች  ጋር የሰላም ውይይት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

አባ ገዳ ጂሎ ማኖ የሰላም እጦት ጎልቶ በሚታይበት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ካለፈው ሰኞ ጀምሮ የሰላም ሳምንት መታወጁን  አስታውሰዋል፡፡

ሰላምን የማይፈልጉና ማንነታቸውን የደበቁ ጥቂት የታጠቁ ግለሰቦች በባህላዊ የገዳ ስርዓት የሚተላለፈውን የሰላም ሳምንት ለማደናቀፍ መንቀሳቀሳቸውን የገለፁት አባ ገዳው "የኦሮሞ ህዝብ የመቻቻል፣ የመከባበርና የመረዳዳት መልካም ባህል ባለቤት እንጂ የመግደልና የማፈናቀል ታሪክ የለውም "ብለዋል፡፡

ሌላው የጉጂ አባገዳ ሚጠጋ ኖቴ የሰላም አዋጁ በአንድ ወር ወይም በአንድ ሳምንት ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ነገ በምስራቅ ጉጂ የሚታወጀው የሰላም ሳምንት የኦሮሞን ህዝብ ተወካዮችን ጨምሮ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና የመንግስት ተዋካዮች በተገኙበት የሚከናወን ይሆናል ።

የኦሮሞ ህዝብ በተለይም ወጣቱ የወላጆችን ፣ የአባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎችን ምክር ተቀብሎ ሰላም በማስፈን በሀገር ግንባታ ላይ እንዲረባረብ መክረዋል፡፡

" ሰላምን የማይፈልግና በሰላም የማይፈታ ችግር የለም " ያሉት አባ ገዳው ሀገር የምትኖረው በመረዳዳት ፣ በመከባበር ፣ በመቻቻልና ተባብሮ በመስራት እንጂ አንዱ ሌላውን በማሳደድ መሆን እንደሌለበት አመልክተዋል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የሰላም መታወክ ችግር በአጭር ጊዜ ወደ ነበረበት ይመለሳል የሚል እምነት እንዳለቸው ገልጸዋል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ ለተራበ የሚያበላ ፣ የተጣላን የሚያስታርቅ ፣ ለዘመናዊም ሆነ ለባህላዊ ህግ የሚገዛ ስልጡን ህዝብ እንደሆነ አመልክተው " ሰላም እንዲሰፍንና የህግ የበላይነትን እንዲከበር የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ለወጣቶች  ምክራችንን በመለገስ  ለሀገራችን ተባብረን  እንስራ "  በማለት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም