ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና እስራኤል በንግድ፣ ኢንሸስትመንትና ቱሪዝም መስክ ያላቸውን ትብብር ማሳደግ እንዳለባቸው ተጠቆመ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 25/2010 ኢትዮጵያና እስራኤል በንግድ፣ ኢንሸስትመንትና ቱሪዝም እንዲሁም በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መስክ ያላቸውን ትብብር በይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባቸው ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለፁ። ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ለእስራኤሉ አቻቸው ሬዩቪን ሪቭሊን ትላንት ምሽት በብሔራዊ ቤተ_መንግስት የእራት ግብዣ አድርገዋል። በዚህ ወቅት ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ እንደተናገሩት፤ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ወደ ሶስት ሺህ ዓመታት የሚጠጋ በንጉስ ሰለሞንና ንግስት ሳባ ወቅት የተጀመረ ነው፡፡ እስራኤል አገር የሚገኙ የኢትዮጵያ አብያተ_ክርስቲያናትና ገዳማት በሁለቱ አገሮች መካከል ጠንካራ የልብ ወዳጅነት እንዲኖር ከማስቻሉም በላይ በህዝብ ለህዝብና በባህል ትስስር ረገድ ጠንካራና ታሪካዊ ወዳጅነት እንዲኖር ማድረጉን ገልፀዋል። 'ኢትዮጵያዊ ማንነት ያላቸው ቤተ እስራኤላዊያን ለሁለቱ አገሮች ጠንካራ ወዳጅነት እንደ ድልድይ ሆነዋል' ብለዋል። ኢትዮጵያ ባወጣችው የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ምክንያት ከአፍሪካ አገሮች መካከል ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች መምጣቷን ተናግረው እስራኤላውያን ባለሃብቶች በዕድሉ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል። ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ሁለቱ አገሮች ያሉበት ቀጠና ሰላምና ደህንነት ያልተረጋገጠበት በመሆኑ በጸጥታ ጉዳዮች ላይም በትብብር መስራት እንደሚገባቸውም እንዲሁ ገልፀዋል። የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ሬዩቪን ሪቭሊን በበኩላቸው የእስራኤል ፕሬዝዳንት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ እሳቸው አራተኛው በመሆናቸው ኩራት እንደተሰማቸው ገልፀዋል። ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ ለረጅም አመታት የዘለቀች ለሌሎች የአፍሪካ አገራትም የነፃነት  ተምሳሌት ተደርጋ የምትወሰድ መሆኗንና ከእስራኤልም ጋር ለረጅም ዘመናት የዘለቀ ጠንካራ የልብ ወዳጅ አገር ናት ብለዋል። እስራኤል በውሃ፣ ቴክኖሎጂ፣ በጤና፣ ግብርና፣ ምግብ ዋስትና፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ሳይበርና ሌሎች የልማት ዘርፎች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራት እንደምትሻም ገልፀዋል። ኢትዮጵያና እስራኤል 116 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ የንግድ ትስስር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2017 ዓ.ም እንደነበራቸው የተገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ። 104 የሚደርሱ የእስራኤል የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ተመዝገበው የሚገኙ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 55 የሚደርሱት በስራ ላይ ሲሆኑ 45 የሚደርሱት ደግሞ ወደ ተግበራ ደረጃ በመሸጋገር ላይ ሲሆኑ በዚህም ለኢትዮጵያዊያን የስራ እድል ፈጥረዋል። ኢትዮጵያና እስራኤል ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1956 ነው። በትላንቱ የእራት ግብዣ ላይ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣የሀይማኖት አባቶችና አባገዳዎች እንዲሁ ታዋቂ ግለሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ነበሩ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም