ፋሲል ከተማና ወልዋሎ አዲግራት ያለጎል ተለያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ፋሲል ከተማና ወልዋሎ አዲግራት ያለጎል ተለያዩ
መቀሌ ታህሳስ 28/2011 በመቀሌ ከተማ ዛሬ በተካሄደው የኢትዮጵያ ፕሪሜር ሊግ እግር ኳስ ውድድር ፋሲል ከተማና ወልዋሎ አዲግራት ባዶ ለባዶ ተለያዩ ።
ውድድሩ ስፖርታዊ ጨዋነትን ጠብቆ የተካሄደ መሆኑን የክለቦቹ አሰልጣኞች ገልፀዋል።
"ውድድሩ ፍፁም ስፖርታዊ ጨዋነት የተሞላበት ነበር" ያሉት የፋሲል ከተማ አሰልጣኝ ሀብታሙ ዟለ በመቀሌ ስታዲየም የታየውን ስፖርታዊ ጨዋነት በጎንደርና ሌሎች ከተሞች ለመድገም እንደሚሰሩም አመላክተዋል።
የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ክለብ አሰልጣኝ ጸጋይ ኪዳነማርያም በበኩላቸው "ጨዋታው ጥላቻ ሳይሆን ፍቅርና አንድነት የታየበት ነበር" ብለዋል።
ጨዋታውን የመሩት የፌደራል ዳኛ አክሊሉ ደግፌ "ጨዋታው ያለምንም ችግር የተጠናቀቀ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ " ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ሁለቱም ክለቦች ዛሬ ባካሄዱት ጨዋታ እኩል 12 ነጥብ ይዘው ወጥተዋል።
ክለቦቹ በመጭው ረቡዕ በመቀሌ ስታድየም የጥሎ ማለፍ ውደድር እንደሚያካሂዱም ታውቋል።
የሁለቱን ክለቦች የዛሬውን ጨዋታ ያስጀመሩት የትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ገነት አፋ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት ሰውነት ቢሻው ሲሆኑ በጨዋታው በሺህዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ታድመዋል።
በሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች መካከልተፈጥሮ በነበረው ግጭት ክለቦቹ ላለፈው አንድ ዓመት ከሜዳቸው ውጭ በገለልተኛ ሜዳ ውድድራቸውን ሲያካሂዱ መቆየታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከአማራና ትግራይ ክልሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ባደረገው ውይይት ክለቦቹ ለአንድ ዓመት ያህል በሜዳቸው አቋርጠውት የነበረን ውድድር እንደገና እንዲጀምሩ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።
በተደረሰው ስምምነት መሰረትም በዛሬው ዕለት ውድድራቸውን በመቀሌ ከተማ አካሂደዋል።