ቀጥታ፡

ትውልድ መቅረጽና የአገር ግንባታ ላይ የሙያ ግዴታችንን እንወጣለን -መምህራን

አዲስ አበባ ታህሳስ 27/2011 ትውልድ የመቅረጽና የአገር ግንባታ ላይ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እንደሚሰሩከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተውጣጡ መምህራን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሶስት ሺህ 600 በላይ የአንደኛ፣ ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት መምህራን ጋር ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙና አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለጹ መምህራን እንደተናገሩት ትውልድ የመቅረጽና አገር ግንባታ ላይ የመምህራን ኃላፊነት እጥፍ ድርብ በመሆኑ ሙያቸው የጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ይሰራሉ።

በአገሪቱ የለውጥ እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ ባለበት ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶችን ለማስወገድ በውይይት የሚያምን ትውልድን ለመፍጠርና ሰላምን ለማስፈን እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

ከሶማሌ ክልል የመጡት መምህርት ሶፊያ አህመድ አንድ መምህር ብዙ ትውልድ ነው የሚያፈራው ይሄንን ትውልድ መምህራን የአገር ፍቅር ካሰረጹ ወጣቱ አገሩን ይጠበቃል ብዬ አስባለሁ ብለዋል፡፡

መምህሩ ሁልጊዜ ማስተማር ያለበት አገራቸውን በፍቅር ፣በሰላም አብረው እንዲኖሩ በማድረግ ነው፡፡  ይህን ተግባር እስካሁን ድረስ እያበረክትን ነበር ከአሁን በኋላም  ይህንኑ እንሰራለን ነው ሉት፡፡

ከአማራ ክልል የመጡት መምህር አግማስ ፈንታው በበኩላቸው "እኛ የምናደርገው ነገር ከቀለም ትምህርቱ ባሻገር መቻቻል እንዳለብን ነው ይሄ ለውጥ ያመጣው ጉዳይ እንደሆነ ወደ አላስፈላጊ ነገር የሚሄዱ ነገሮች አሉ መመለስ እንዳለብን በዩንቨርስቲዎች ተቻችለን መማር እንዳለብን ለአገር ዕድገት የሚበጀው መቻቻል መሆኑን ማስተማር እንዳለብን ነው ምረዳው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር የውጭና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጫንያለው ታፈሰወርቅ በበኩላቸው ትምህርት ቤት ላይ አገር ይገነባል አገር ይፈርሳል የመምህራን ሚና ከፍተኛ ነው ህጻናት እንደሰጠናቸው ይሆናሉ ሀገርን ስለ መገንባት የምናስተማራቸው ከሆነ ሀገር ይገነባሉ ስለ ሰላም የምናስተምራቸው ከሆነ ሰላምን ያሰፍናሉ ከዛ ውጭ ስለ ጎጥ የምናስተምራቸው ከሆነ ጎጠኛ ይሆናሉ ስለዚህ የእኛ የመምህራን ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ከጥቅሞቻችን በላይ የአገር ሰላም ያሳስበዋል። የእኛ መምህርነት ሙያችን ሰፊ ነው ግን ደግሞ እንደ ሰው መኖር አለብን እንደ ሰው ለመኖር የሚያስችለውን ነገር ሊደረግ ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በትውልዱ ዘንድ ያለውን የተዛባና አሉታዊ አመለካከት መቀየር እና የስብዕና ግንባታ ላይ የመምህራን ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

"ከመወያየት ከመነጋገር ይልቅ በግጭት፣ በጦርነት የማመን አመለካከትን የያዘውን የአዕምሮ ትጥቅ ማስፈታት የእናንተ እንጂ የእኔ ኃላፊነት አይደለም" ሲሉም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት ትውልዱን ለአገር ግንባታ ጠቃሚ የሆኑ ታሪኮችን ማስተማርና ማነጽ፣ መምራትና የወደፊቱን ማመላከት የመምህራን ድርሻ ነው።

መንግስት ለትምህርት ዘርፉ ትኩረት በመስጠት በሁለት የሚኒስቴር መስሪያ ቤት እንዲመራ መደረጉና እየተዘጋጀ ያለው የትምህርት ፍኖተ-ካርታ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል መሆኑንም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም