ቀጥታ፡

የአማራ ክልል ህዝብ ከሚያከብራቸው የኃይማኖት አባቶች ጋር ለሰላም ይሰራል---አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

ባህርዳር ታህሳስ 27/2011 የአማራ ክልል ህዝብ የኃይማኖት አባቶችን የሚያከብርና በመስዋዕትነት ለተገኘው ለውጥ ቀጣይነት አብሮ የሚሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ።

ርዕሰ-መስተዳደሩ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂ አባቶች ጋር በክልሉና በሃገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይም አቶ ገዱ እንደተናገሩት የአማራ ክልል ህዝብ የእምነት አባቶቹን የሚያከብርና ፈቃዳቸውንም ለመፈጸም የማያቅማማ ነው።

በሃገሪቱ እየታየ ላለው ለውጥ በርካቶች መስዋዕትነት እንደከፈሉ ተናግረው ለውጡ አንዱን ተጠቃሚ ሌላውን ተጎጂ የሚያደርግ በማስመሰል ለህዝብ የማይጠቅም አሉባልታ እየተላለፈ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለዘመናት በደምና በአጥንት ተሳስሮ የኖረውን የኢትዮጵያ ህዝብ እርስ በእርስ ለማቃቃር የሚደረጉ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ለአላስፈላጊ ጥርጣሬና ለሰላም መታወክ ምክንያት እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በተለይም በባህል፣በእምነት፣በሃይማኖት እና በታሪክ የጋራ ማንነት ያላቸውን የአማራና የትግራይ ወንድማማች ህዝቦች በጥርጣሬ እንዲተያዩ ለማድረግ የሚሞክሩ ተግባራትም ተገቢነት እንደሌላቸው ጠቁመዋል።

"የሃይማኖት አባቶች በሁለቱም ክልሎች ላይ የሚስተዋለውን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ  አካሄዱ አላማረም የምትሉትን ልትመክሩና ልትገስጹ ይገባል" ያሉት አቶ ገዱ የአማራ ክልል ህዝብም ችግሮች የሚፈቱት በህግና በስርዓት መሆኑን እንደሚያምን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያርክና የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንደገለጹት መሪዎች በህዝቦች መካከል መተማመንን መፍጠር ካልቻሉ እየበደሉ መሆናቸውን ሊያውቁት ይገባል።

የኢትዮጵያ ህዝብ የየራሱ የሆነ የብሄር ማንነት ቢኖረውም ሁሉም እርስ በዕርሱ በባህል፣በሃይማኖት በጋብቻና በሌሎችም ጉዳዮች የተሳሰረና የማይነጣጠል መሆኑን ተናግረዋል።

"ስለሆነም ይህንን ህዝብ ለመነጠል የሚለፋ የፖለቲካ መሪም ይሁን ማናቸውም አካላት ጊዜያዊ ብጥብጥ ከመፍጠር ባለፈ አንድ የሆነን ህዝብ መነጠል አይቻልም" ብለዋል።

"የሃይማኖት ተቋማትም የማያልፉትን ሀገርንና ተቋማትን ዘንግተው ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ህዝብን ለማቃቃርና ሰላምን ለማጠልሸት የሚሰሩ አካላትን ይመክራሉ፣ይገስጻሉም" ነው ያሉት።

"የዘመኑ የሀገሪቱ ፖለቲከኞች ዋነኛ ተልኳቸው መጀመሪያ ሰላምን መስበክ ስለሆነ  ስላም ከእቅፍ ውስጥ እንዳትወጣ ሮጦ መያያዝ ያስፈልጋል"ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ  ካርዲናል ብፁዕ አቡነ ብርሃነ እየሱስ ናቸው።

"ህዝብን የሚመራ በየደረጃው ያለ ማንኛውም አካል ስለ ልማት ማውራት ከመጀመሩ በፊት የልማትን መሰረት ሰላምን እጥብቆ ሊይዝ ይገባል" ብለዋል።

እንደ ሀገር እየታየ ያለው ለውጥ ሰላምን ፣ በጋራ መስራትንና መጠቀምን መርህ ያደረገ ስለሆነና ለኢትዮጵያዊያንም ከዚህ የተለየ አማራጭ ስለሌለ ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ አስረድተዋል።

በውይይቱ ላይ የሀገር ሽማግሌዎችና ከሁሉም የእምነት ተቋማት የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም