ቀጥታ፡

በባህር ዳር ከተማ የሰላም ኮንፈረንስ ተካሄደ

ባህር ዳር ታህሳስ 27/2011 ሰላም ለኢትዮጵያዊያን የመብትና የግዴታ ጉዳይ ሳይሆን አማራጭ የሌለው የጋራ ሀብት መሆኑን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ  የበላይ ጠባቂ አባቶች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂ አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ማህበር ትናንት በባህር ዳር ከተማ የሰላም ኮንፈረንስ አካሂደዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተህዶ ቤቴ ክርስቲያ የውጭ ግንኙነት የበላይ ኃላፊና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ የጋራ ሀብት ለሆነው ሰላም መጠበቅ የሃማኖት ተቋማት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለሰላም መደፍረስ ምክንያት ለሆኑ የህዝብ ጥያቄዎች መንግስት አፋጣኝ መልስ መስጠት እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

''የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት  ህዝቡን ማወያየት ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው'' ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤቴክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ አባ ሀጎስ ሀይሽ ናቸው።

''የኢትዮጵያ ህዝብ  በአሁኑ ወቅት ሰላምን ይሻል'' ያሉት አባ ሀጎስ ሰላምን ለማስጠበቅ የሃይማኖት አባቶች በየእምነት ተቋማት ምእመናን የማወያየት ስራ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ ዋና ጸሐፊ መጋቢ ዘሪሁን ደጉ በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያን አንድ ሲሆኑ አለምን ያስደመመ ታሪክ መስራት ይችላሉ።

የሃይማኖት አባቶችም ሆኑ የመንግስት አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት ለእምነቱ ታዛዥ የሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ ነበረ መተሳሰቡና ክብሩ መመለስ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

በሃይማኖትም ሆነ በብሔር በህዝቡ መካከል መከፋፈል ሲፈጥሩ የነበሩ አካላት  የማንኛውንም እምነት የማይወክሉ  መሆናቸውን የጉባኤው የበላይ ጠባቂ አባል ሸክ አህመድ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች ማህበር አባል ዶክተር ወርቁ ነጋሽ ብሄር ብሄረሰቦችን ለማጋጨት የሚደረገውን ጥረት  መላ የኢትዮጵያ ህዝብ በጋራ ሊያወግዘው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም