የመምህራን ጥያቄ በለውጡ ሂደት እየተፈታ ይሄዳል-- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
የመምህራን ጥያቄ በለውጡ ሂደት እየተፈታ ይሄዳል-- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ
አዲስ አበባ ታህሳስ 27/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መምህራን ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች በዘርፉ እየተካሄደ ያለው ለውጥ ችግሩን በቀጣይ እየፈታው ሊሄድ እንደሚችል ገለፁ።
በአሁኑ ጊዜ የመምህራንን ህይወት በቅጡ ሊለውጥ የሚችል የደመወዝ ጭማሪ ማድረግ ባይቻልም በአገሪቷ ያለው የለውጥና እድገት ተስፋ በጊዜ ሂደት ችግሩን ሊፈታው ይችላል ብለዋል።
ለዚህም መንግስት ትኩረት በመስጠቱ ዘርፉ በሁለት የሚኒስቴር መስሪያ ቤት እንዲመራ እንዲሁም የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ውይይት እየተደረገበት መሆኑን ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመላ አገሪቱ ከተውጣጡ 3 ሺህ 700 ከሚሆኑ የአንደኛ፣ ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት መምህራን ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ መምህራኑ በደመወዝና ጥቅማጥቅም፣የትምህርት ግብአት አቅርቦት፣ የትምህርት ጥራት መጓደልን፣ በፀጥታ መጓደል ጉዳይ በተማሪዎችና መምህራን ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር አስመልክቶ በጥያቄ መልክ አንስተዋል።
መምህራኑ እንደሚሉት የሁሉም ነገሮች የእውቀት መሰረት መምህር ሆኖ ሳለ በመንግስት በኩል የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው ፤ ደመወዝና ጥቅማጥቅሙም ዝቅተኛ ነው ብለዋል።
የመምህራን መኖሪያ ቤት ጉዳይ፣ የትምህርት እድል በበቂ ሁኔታ አለመመቻቸትና ዘርፉ የእውቀት ከመሆን ይልቅ የፖለቲካ መድረክ መሆኑ እያመዘነ መምጣቱንም ጠቁመዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የግብአት ፣ ሂደትና ውጤት ወሳኝ ቢሆንም በተለይ የተሟላ ሰብአዊ ግብአት እንዲኖር በማድረግ በኩል ተዘንግቷል የሚል ጥያቄ ተነስቷል።
በአገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለው ግጭት የመምህራንን ህይወት እየቀጠፈ፣ ቤትና ንብረታቸውን እያወደመ በመሆኑ መንግስት ህግ የማስከበር ስራውን እንዲሰራም ጠይቀዋል።
መምህራኑ በጥያቄያቸው የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነት ይዘት ምን እንደሚመስል እንዲሁም ወልቃይትን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ስለሚነሱ ግጭቶች መንግስት መፍትሄ ሊያበጅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ለህዳሴው ግድብ ድጋፍ ለማድረግ መምህራኑ የፈፀሙት የቦንግድ ግዥ ገንዘቡ ለትክክለኛው አላማ የመዋሉ ጉዳይ እንደሚያሳስባቸውም አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መምህራኑ ላነሷቸው እነዚህና ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስተሩ እንዳሉት መንግስት የትምህርቱን ሴክተር ለማሳደግና ለማዘመን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል።
የትምህርቱ ዘርፍ በሁለት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት እንዲመራ መደረጉ እንዲሁም የትምህረት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ውይይት እየተደረገበት መሆኑ ትኩረት ለመሰጠቱ ማሳያ ነው ብለዋል።
አገሪቷ ብዙ የእድገትና የለውጥ ተስፋ ስላላት መምህራን የሚያነሷቸው ጥያቄዎች በሂደት ሊፈቱ እንደሚችሉ አመላክተዋል።
በዚህ ሂደት ውስጥ የትምህርት ጥራትና የመምህራን ተጠቃሚነት እየተሻሻለ እንደሚመጣ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
ከሰላም አንፃር የጦርነት ትጥቅ ያለው ጭንቅላት ውስጥ በመሆኑ በሁሉም ዘንድ የግጭትና የጦርነት ትጥቆች ከጭንቅላት መፈታት ይኖርበታል ነው ያሉት።
"ኢትዮጵያ ውስጥ በ3 ወይም በ5 ወራት ውስጥ መንግስት እሆናለሁ ብሎ ማሰብ ቅዥት ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምርጫና በሃሳብ የበላይነት አሸናፊ ለመሆን መዘጋጀት ያስፈልጋልም ብለዋል።
የትምህረት ተቋማት የውይይትና ክርክር መድረክ እንጂ የግጭት አካባቢዎች መሆን የለባቸውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስተሩ ለዚህም መምህራን ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
መምህራን የአገርን ምንነት በቅጡ የሚረዱ በመሆናቸው አገሪቷን ከመፍረስ አደጋ በመጠበቅ የሰላም አምባሳደር በመሆን ከፊት መቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በሃሳብ የበላይነት፣በንግግር እንዲሁም አንዱ በሌላው ውስጥ መሆኑን የሚያምን ዜጋ በመፍጠር የመምህራን ሚና የጎላ መሆኑንም ጠቅሰዋለ።
"ታላቁን የህዳሴ ግድብ እንደጀመርነው ሁሉ መጨረስ እንደምንችል ማሳየት አለብን" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስተሩ ለዚህም ሁሉም ዜጋ አስተዋፆውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለፁት በማንነት ጉዳይ የሚነሱ ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ጥናት የሚያደርግ አካል ቷቋቁሟል።
የኢትዮ- ኤርትራን እርቅ በሚመለከት ዋናው ጉዳይ የሁለቱ አገራት ህዝቦች መገናኘት ቢሆንም ቀጣይ ለሚደረጉ ውይይቶች በሁለቱም በኩል የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሟል።