የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በተካሄዱ ጨዋታዎች ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በተካሄዱ ጨዋታዎች ተጀመረ
አዲስ አበባ ታህሳስ 27/2011 የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተካሄዱ ጨዋታዎች ተጀመረ።
የዘንድሮው የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር አዲስ ተሳታፊውን ጎንደር ከተማ ጨምሮ 10 ክለቦች ይሳተፉበታል።
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ዐቃቤ ነዋይ አቶ ሰጠኝ አዲሱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፕሪሚየር ሊጉ ሲካሄድ የፌዴሬሽኑ ዋንኛ የትኩረት አቅጣጫ ስፖርታዊ ጨዋነት በውድድር ሜዳዎች እንዲሰፍኑ ማድረግ ነው።
ባለፈው ዓመት በሊጉ የታየ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ዘንድሮ እንዳይደገም ፌዴሬሽኑ ከክለቦችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞችና ደጋፊዎች ስፖርታዊ ጨዋነትን መላበስና ለስፖርታዊ መርሆዎች ተገዢ መሆን እንዳለበቸው አሳስበዋል።
የዘንድሮው ዓመት የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ታህሳስ 6 ቀን 2011 ዓ.ም ይጀመራል ቢባልም "ክለቦች በቂ ዝግጅት ባለማድረጋቸውና የክለቦች ምዝገባ በሚፈለገው ጊዜ ባለመጠናቀቁ" ውድድሩ ዘግይቶ ተጀምሯል ብለዋል።
ዛሬ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊጉ ሲጀመር በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች ተደርገዋል።
የመጀመሪያው ጨዋታ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ሲሆን ኮልፌ ቀራኒዮ 30 ለ 27 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
በሁለተኛው መቐለ ሰብዓ እንደርታን ያስተናገደው ፌዴራል ፖሊስ 27 ለ 25 ተሸንፏል።
በክልል ዱራሜ ላይ ከምባታ ዱራሜ ከመከላከያ ያደረጉት ጨዋታ በመከላከያ 32 ለ 26 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ አዲስ ተሳታፊውን ጎንደር ከተማ 15 ለ 14 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
ነገ የሊጉ ቀሪ አንድ ጨዋታ የሚካሄድ ሲሆን የአምናው የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወደ ቡታጅራ በማቅናት ከቡታጅራ ከተማ ጋር ይጫወታል።
የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሶስተኛ የውድድር ዓመቱ ነው።
ፕሪሚየር ሊጉ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ሲሆን፤ መከላከያ የ2009 ዓ.ም፤ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ደግሞ የ2010 ዓም የሊጉ አሸናፊዎች መሆናቸው ይታወሳል።