የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ነዋሪዎች በኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት በቂ አገልግሎት እንደማያገኙ ገለፁ - ኢዜአ አማርኛ
የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ነዋሪዎች በኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት በቂ አገልግሎት እንደማያገኙ ገለፁ
ሽሬ እንዳስላሴ ታህሳስ 27/4/2011 የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ነዋሪዎች በኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት በቂ አገልግሎት እንደማያገኙ ገለጹ።
ተቋሙ በበኩሉ በነዋሪዎቹ የቀረቡ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ከአደረጃጀት ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎች መውሰድ መጀመሩን አስታውቋል።
በኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የተቋሙ የስራ ኃላፊዎች ትናንት ከከተማው ነዋሪዎች ጋር ምክክር አካሂደዋል፡፡
የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች ካነሱዋቸው ችግሮች መካከል ለረዢም ዓመታት ያገለገሉ የኤሌክትሪክ መስመር ተሸካሚ ምሶሶዎች በእርጅና ምክንያት እየወደቁ ተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥ ማጋጠም ተጠቃሽ ነው።
እንዲሁም በየቦታው የተተከሉ ትራንስፎርመሮች በየጊዜው መቃጠልን ተከትሎ የኤሌክትሪክ ኃይል በመቋረጥ በእለታዊ ኑሮአቸው ላይ ጫና እየፈጠረባቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም የተጠቀሙበት የኤሌክትሪክ ኃይል በወቅቱ ሰለማይነበብ ተጠራቅሞ በአንዴ የአገልግሎት ክፍያ እንዲፈጽሙ እንደሚጠየቁም ተናግረዋል።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን ተመዝግበው ቆጣሪ ለማግኘት ከአራት ዓመት በላይ እንደሚጠብቁ የመድረኩ ተሳታፊዎች ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ብልሽትና አደጋ ሲያጋጥምም የዲስትሪክቱ ባለሙያዎች ቶሎ ያለመድረስ ችግር እንዳለባቸው አስታውቀዋል፡፡
የዲስትሪክቱ ሰራተኞች የአገልጋይነት መንፈሳቸው የወረደና የስነ ምግባር ችግር ያለባቸው መሆኑም ነው ነዋሪዎቹ ያስታወቁት።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የትግራይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ገብረመድህን እንዳሉት ተቋሙ አደረጃጀቱንና አሰራሩን በማዘመን አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ቀደም ሲል በክልል ደረጃ በመቀሌ ከተማ ብቻ የነበረው የተቋሙ ሁለተናዊ አገልግሎት ለትግራይ ማእከላዊ፣ ሰሜናዊ ምዕራብና ምዕራብ ዞኖች ተደራሽ ለማድረግ ከአንድ ወር በፊት በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ አዲስ የደንበኞች አገልግሎት መክፈቱን ገልጸዋል።
በአገልግሎት ብዛት በየጊዜው ችግር እየፈጠሩ ያሉት የኤሌክትሪክ መስመር ተሸካሚ ምሶሶዎችን ደረጃ በደረጃ ወደ ኮንክሪት ለመቀየር እንቅስቃሴ መጀመሩንም አቶ መስፍን ተናግረዋል።
እስከዛው ግን ነዋሪዎች ከዛፍ ጋር ንኪኪ ያላቸው ምሶሶዎችን ከአደጋ ለመከላከል ዛፉን በመቁረጥ የሃይል መቆራረጥን መከላከል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በከተማው የሚታየው የትራንስፎርመር እጥረት ለማቃለል ከ800 በላይ ትራንስፎርመሮች ግዥ በሂደት ላይ መሆኑንና ከዚህ ጎን ለጎን የተቃጠሉትን ትራንስፎርመሮች የመጠገን ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
''እስካሁንም ከ60 በላይ ትራንስፎርመሮች ተጠግነው ለአገልግሎት በቅተዋል'' ብለዋል።
የቆጣሪ እድላ ከትራንስፎርመር ተከላ ጋር የሚያያዝ በመሆኑ የትራንስፎርመር ግዥ ከተፈጸመ በኋላ የሚሟላ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በትግራይ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሽሬ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ግደይ በየነ በበኩላቸው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ቆጣሪ በወቅቱ ያለማንበብ ችግርን በጊዚያዊነት ለመፍታት የአንባቢ ሰራተኞች ቁጥር ለመጨመር ቅጥር እንደሚካሄድ ገልፀዋል፡፡
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ደግሞ ደረጃ በደረጃ በካርድ በሚሰራ ቆጣሪ የመተካት ስራ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡
የተቋሙ ሰራተኞች የአገልጋይነት መንፈስና የስነ ምግባር ችግር በሚካሄደው አዲስ አደረጃጀት እንደሚፈታ ተናግረዋል፡፡