ሰላምን በማረጋገጥ በኩል መምህራን ጉልህ ሚና አላቸው ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምን በማረጋገጥ በኩል መምህራን ጉልህ ሚና አላቸው ተባለ
አዲስአበባ ታህሳስ 26/2011 በአገሪቷ ሰላም እንዲሰፍን በማደረግ በኩል መምህራን ጉልህ ሚና እንዳላቸው የኢፌዲሪ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ገለፁ።
ሚኒስትሯ መምህራን ለአገር ሰላም ያላቸውን ሚና አስመልክቶ ከመምህራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ውይይት አድርገዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ሃይለየሱስ ታዬ ለውይይት ያቀረቡትን መነሻ ፅሁፍ ተከትሎ መምህራን ለሰላም ያላቸውን አስተዋፆ በሚመለከት ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።
የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት በአገሪቷ ሰላም እንዲሰፍን በማደረግ በኩል መምህራን ጉልህ ሚና አላቸው።
በእውቀት የታነፀና ታሪክን በትክክለኛው መንገድ የሚረዳ ዜጋ ለማፍራትም የመምህራኑ ድርሻ የማይተካ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም መምህራን ታሪክን በተሳሳተና በተዛባ መንገድ በማስተላለፍ ጠላትነትን ማስተማር እንደሌለባቸው አስገንዝበዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላየ ጌቴ በበኩላቸው መምህራን የተለዩ ጥያቄዎች ቢኖሯቸውም በአሁኑ ወቅቱ የአገሪቷ ሰላም ጉዳይ አብይ አጀንዳ በመሆኑ የሰላም መፍትሄ አካል በመሆን የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።
በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች በሚታየው ግጭት በተለይ ተማሪዎች፣መምህራንና የትምህርት ተቋማት ተጎጂዎች መሆናቸውንም ገልፀዋል።
የታሪክ ምሁራንም ትክክለኛውን የኢትዮጵያ ታሪክ በመፃፍ ብሎም በማስተማር አገራዊ ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል ዶክተር ጥላየ።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሪዘዳንት አቶ ዮሃንስ በንቲ በበኩላቸው በአገሪቷ ለሚታየው ለውጥ መምህራን የበኩላቸውን እገዛ ያደርጋሉ ብለዋል።
በትምህርት ተቋማትም ይሁን በማህበረሰቡ ዘንድ ለሚፈጠሩ ግጭቶች መምህራን የሰላም አካል በመሆን እንደሚሰሩም ገልፀዋል።
ለዚህም መምህራኑ አደራን ተቀባይ በመሆን እንደሚሰሩ አቶ ዮሃንስ አረጋግጠዋል።