ካህናት የህዝቡን ሰላም በመጠበቅ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ካህናት የህዝቡን ሰላም በመጠበቅ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ
አምቦ ታህሳስ 26/2011 የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ካህናት ለህብረተሰቡ ሰላምን በመስበክ ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር የድርሻቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ሊቀ-ጳጳስ አቡነ ኤጲፋንዮስ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ቤተ-ክርስቲያኗ በምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በአምቦ ከተማ ለሶስት ቀናት ያዘጋጀችው የሠላም ኮንፈረንስ ዛሬ ተጠናቋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤጲፋንዮስ በኮንፈረንሱ ማጠናቀቂያ ወቅት እንደተናገሩት በሀገሪቱ ሠላም ነግሶ ለፍቅርና አንድነት ሁሉም በህብረት መትጋት ይኖርበታል፡፡
በተለይ የኃይማኖት መሪ የሆኑ ካህናት ወጣቶች ከስሜታዊነት ወጥተው ምክንያታዊ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ሰላምን በመስበክ ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ እየሆኑ ያሉ የመፈናቀልና የእርስ በእርስ ግጭት ለማስቀረት ቤተ-ክርስቲያኗ ከመንግስት ጎን በመቆም እንደምትሰራም አረጋግጠዋል፡፡
" የዓለም ህዝብ ሁሉ ከአንድ ዘር አዳምና ሄዋን ነው የተፈጠረው፣ ስለዚህም አንዱ ከሌላው ጋር በፍቅርና በመተሳሰብ አብሮት ሊኖር ይገባል እንጂ ፍቅርን በግብዝነት ማበላሸት አይገባም " ብለዋል፡፡
በመንግስት ስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ባለስልጣናትም ሆኑ የህዝብ አገልጋዮች ለህዝባቸው ትህትና የተሞላበት አገልግሎት መስጠት እንደሚኖርባቸውም መክረዋል፡፡
ባለስልጣናት ራሳቸውን ከሙስና ጠብቀው ለህብረተሰቡም ሙስና ጰያፍ እንደሆነ በማስተማር ኃላፊነታቸውን በተገቢው እንዲወጡም እንዲሁ፡፡
ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መካከል ሊቀ ህሩያን ዳዊት ታደሰ የሀገሪቱ ህዝቦች ከቀደመው ጊዜ ጀምሮ በሰላምና በፍቅር ተዋደው አብረው የኖሩት ዘላቂነት ሆኖ እንዲቀጥል የኃይማኖት አባቶች ሊሰሩ እንደሚገባ መልክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
" የኃይማኖት አባቶች ስለ ህዝቦች ሰላምና አንድነት ከኮንፈረንሱ የተገነዘብነውን ለምዕመናን ማድረስ ተቀዳሚ ስራችን ይሆናል" ብለዋል፡፡
ሌላው የኮንፈረንሱ ተሣታፊ የአምቦ ከተማ ነዋሪው አቶ ግርማ አባድረስ በበኩላቸው ቤተ ክርስቲያኗ ለህዝቡ ስለ ሰላም ለማስተማር ይህን ኮንፈረንስ በማዘጋጀትዋ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እሳቸውም ከቤተ ክርስቲያኗ ጎን ቆመው ስለ ሰላም በተለይ ወጣቱን ትውልድ ለማስተማር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በኮንፍረንሱ በምዕራብ ሸዋ ሃገረ ስብከት ስር የሚገኙ ካህናት፣ ወጣቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ከፍሎች ተሳትፈዋል፡፡