ቀጥታ፡

በእቅድ ዘመኑ የተመዘገበው የግብርናው ዘርፍ ዝቅተኛ እድገት በቀጣይ እንደሚካካስ ተገለጸ

አዳማ ታህሳስ 26/2011 በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የሶስት ዓመታት አፈፃፀም ውስጥ የግብርናው ዘርፍ ዝቅተኛ እድገት በቀጣይ ለማካካስ እየተሰራ መሆኑን  የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በእቅዱ  አፈጻጸም ዙሪያ ለመምከር የተዘጋጀ  መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

በመድረኩ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት በነበሩ ክፍተቶች በዘርፉ የተመዘገበውን እድገት ዝቅተኛ ነው፡፡

የተናበበ አደረጃጀት አለመኖር ፣የአሰራር ኋላቀርነት፣የማስፈፀም አቅም ውስንነት፣የቴክኖሎጅ አቅርቦትና በሀገሪቱ  የተከሰተው ድርቅ ከነበሩት ክፍቶች መካከል  ይገኙበታል፡፡

በአሁኑ ወቅት ክፍተቶችን በመሙላት የተሻለ እድገት ለማስመዝገብ  እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡

ስራውም የዘርፉን ፖሊስና ስትራቴጂዎች ፣የግብርና ልማትና እድገት ፓኬጆችን ከመከለስና ከመፈተሽ ጀምሮ አደረጃጀቶችን በማስተካከል ወደ ሙሉ ትግበራ መግባታቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የመድረኩ ዓላማ በዘርፉ የታየውን ዝቅተኛ ክንውን ከፖሊሲ አውጭዎች ጋር በመገምገም በቀጣይ ጊዜያት ለማካካስ የሚያስችል የጋራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው" ብለዋል።

በ2010/2011 የምርት ዘመን የሰብል ልማት የተሻሻለውን የግብርና ልማትና ዕድገት ፓኬጅ           መሰረት በተከናወነው ስራ 374 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚገኝና  አጠቃላይ የዘርፉ እድገት ከ8 በመቶ በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

በሚኒስቴሩ የእቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ዜና ሀብተወልድ በበኩላቸው የሁለተኛው የግብርና ልማት እቅድ ያለፉት ዓመታት  አፈፃፀም አማካይ እድገት ከ4 መቶ ያልዘለለ እንደሆነ ተናግረዋል።

በ2008 ዓ.ም 2 ነጥብ 3 በመቶ፣ በቀጣዩ ዘመን ደግሞ  6 ነጥብ 7 በመቶ እንዲሁም ባለፈው  ዓመት 3 ነጥብ 5 በመቶ ዝቅተኛ እድገት መመዝገቡን ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት በመስኖና የሰብል ምርት የተሻለ አፈፃፀም ቢመዘገብም  በእንሳስትና ዓሣ ሀብት ልማት፣በቴክኖሎጂ አቅርቦትና ሥርጭት፣ በሜካናይዜሽንና  አሰራር በማዘመን የመጣው ለውጥ ዝቅተኛ ነው።

በተያዘው የበጀት ዓመት አደረጃጀቶችንና አሰራርን ለማዘመን በተደረገው ጥረት   ከ16 ሚሊዮን በላይ  አርሶ አደሮች የተሻሻለው የግብርና ልማትና እድገት ፓኬጅ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"በዚህም በምርምር ውጤቶችና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣በማሳ ዝግጅትና አዝዕርት እንክብካቤ፣የግብዓት አቅርቦትና የአቅም ክፍተት ለማስተካከል የተሻለ እንቅስቃሴ የተደረገ ነው" ብለዋል።

የአፈርና ውሃ እቀባ፣መስኖ ልማት፣የበልግ አዝመራና የቀጣዩ ዓመት የመኽር እርሻ ዝግጅት ከወዲሁ  ትኩረት ያገኙ ተግባራት ናቸው ።

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈፃፀም መጨረሻ በዋናዋና ሰብሎች ከ406 ሚሊዮን ኩንታል በላይ በማምረት የግብርና ዘርፉን እድገት 13 በመቶ ለማድረስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡

በእቅዱ  አፈጻጸም ዙሪያ ለመምከር ለሁለት  ቀናት በተዘጋጀው መድረክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርናና አካባቢ አየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎችም ባለደርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም