በአቶ ዓለም ፍጹም ላይ አቃቤ ሕግ የጠየቀውን ተጨማሪ ክስ የመመስረቻ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ፈቀደ - ኢዜአ አማርኛ
በአቶ ዓለም ፍጹም ላይ አቃቤ ሕግ የጠየቀውን ተጨማሪ ክስ የመመስረቻ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ፈቀደ
አዲስ አበባ ታህሳስ 26/2011 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአቶ ዓለም ፍጹም ላይ አቃቤ ሕግ የጠየቀውን ተጨማሪ ክስ የመመስረቻ አምስት ቀናት ፈቀደ።
ተጠርጣሪው አቶ ዓለም ፍጹም ከሪቬራ ሆቴል እና ፒ ቪ ሲ ፕሮፋይል ማምረቻ ፋብሪካ ሽያጭ ጋር በተያያዘ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ የዓለም ገነት ቆርቆሮ ፋብሪካ ባለቤት ናቸው።
አቃቤ ህግ ከዚህ በፊት በተጠርጣሪው ላይ ክስ ለመመስረት ከችሎቱ 10 ቀናት ያስፈቀደ ቢሆንም ከሌሎች በተመሳሳይ መዝገብ ከሚካተቱ ተጠርጣሪዎች ጋር ክሱን ለማደራጀት እንዲችል ተጨማሪ ጊዜ እንዳስፈለገው ነው ዛሬ ለፍርድ ቤቱ ያስታወቀው።
የተጠርጣሪው ጠበቆች በበኩላቸው "ችሎቱ ቀድሞ በቂ ነው" ብሎ ያመነበትን የክስ መመስረቻ ቀን ለአቃቤ ህግ የፈቀደ ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ክስ መመስረት ባለመቻሉ "ተጠርጣሪው በዋስ ሊፈቱ ይገባል" ሲሉ ተከራክረዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ችሎቱም ቀድሞ የተሰጠው የ10 ቀን የክስ መመስረቻ ብቻ መሆኑን ከግምት በማስገባት የተጠየቀውን የአምስት ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ፈቅዷል።
በመሆኑም ከታህሳስ 26 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ታሳቢ አድርጎ በአምስት ቀናት ውስጥ አቃቤ ሕግ ክሱን አደራጅቶ ለጥር 02 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲቀርብ ብይን ሰጥቷል።
በተያያዘ ዜና ችሎቱ በእነ ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁርንዲ መዝገብ ከተካተቱት 10ኛ ተጠርጣሪ ኮሎኔል ያሬድ ሃይሉ እና 16ኛ ተጠርጣሪ ሻለቃ ሰለሞን በርሄን በተመለከተ መርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል።
ነገር ግን ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው ጊዜ ተገቢውን ስራ ባለማከናወኑ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሳይፈቀድ ተጠርጣሪዎቹ እያንዳንዳቸው በ50 ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ወስኗል፤ ተጠርጣሪዎቹ ከአገር እንዳይወጡ እግድም ተጥሎባቸዋል።