የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ስራ ሊጀምር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ስራ ሊጀምር
አዲስ አበባ ታህሳስ 26/2011 በዲያስፖራ ጉዳይ ትኩረት ያደረገው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ስራ ለመጀመር የመዋቅርና የህግ ማዕቀፍ ተግባር ማጠናቀቁን ገለጸ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ዲያስፖራው መብቱን በማክበር ግዴታውን መወጣት በሚያስችል መልኩ ማዋቀርና የህግ ማዕቀፍ ተሰርቷል።
በዚህም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን በማክበር በአገሩ ልማት የመሳተፍ ግዴታውን እንዲወጣ ስራዎችን ያከናውናል ነው ያሉት።
ኤጀንሲው ቀደም ሲል የነበሩ የአሰራር ክፍተቶችንና የአቅም ማነስን በማስተካከል ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራም ዋና ዳይሬክተሯ አብራርተዋል።
ለዚህም የክልል ዲያስፖራ ማስተባበሪያ ቢሮዎችን በማጠናከርና ድጋፍ በማድረግ አብሮ ይሰራል ነው ያሉት።
ኤጀንሲው በተለያዩ የውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን በህግና ፖሊሲ ማውጣት ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸውም ይሰራል።
ዳያስፖራው በንግድና ኢንቨስትመንት ተሳትፎ የሚያጋጥሙት የአሰራር ችግሮች ከሚመለከታቸው ጋር በትብብር ለመፍታት አሰራር እንደሚዘረጉ ተናግረዋል።
ዲያስፖራውን በተመለከተ መንግስት የሚያወጣቸውን ፖሊሲና አሰራሮችን በየጊዜው ለዲያስፖራው ማሳወቅ ኤጀንሲው ሌላኛው በትኩረት የሚሰራበት ተግባር ነው።
ኤጀንሲው የዲያስፖራውን የመምረጥ መብት እስከማስከበር ይሄዳልም ተብሏል።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ ኤጀንሲው በሰራው መዋቅር መሰረት ሰራተኞችን አሟልቶ በቅርቡ ስራ የሚጀምር ሲሆን ትክክለኛ ጊዜውን በቀጣይ እናሳውቃለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ከሁለት ወራት በፊት የተቋቋመ ሲሆን ከዲያስፖራው የሚገኘውን የዕውቀትና ክህሎት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የኢንቨስትመንትና ንግድ ተሳትፎን ማስተባበርና እገዛ ማድረግ ከተሰጠው ስልጣንና ተግባር መካከል ይጠቀሳል።
በተለያዩ የዓለም አገራት ከሶስት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን እንደሚገኙ የኤጀንሲው መረጃ ያሳያል።
በኢትዮጵያ እስካሁን በዲያስፖራው ጉዳይ ማህበራትና ማስተባበሪያ ቢሮዎች እየሰሩ ሲሆን መንግስትን በመወከል ኤጀንሲ አልነበረም።