ቀጥታ፡

ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር መንስኤና የአዘዋዋሪዎች ማንነት ላይ ጥናት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ታህሳስ 26/2011በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ምንጭና የዋና አዘዋዋሪዎቹን ማንነት ለመለየት ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስታወቀ።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ አገራት ገንዘቦች በሕገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ መያዙንና ዝውውሩ እየጨመረ መምጣቱን ገልጿል።

በጠቅላይ አቃቤ ሕግ የተደራጁ፣ ድንበር ተሻጋሪና አገራዊ ጉዳት የሚያስከትሉ ወንጀሎች ዳይሬክተር አቶ ፈቃዱ ጸጋ ለኢዜአ እንደገለጹት ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር መበራከቱን ተከትሎ ምንጩን፣ መንስኤውንና የሚያዘዋውሩ ወንጀለኞችን ማንነት በሚመለከት ጥናት እየተካሄደ ነው።

ጥናቱን የሚያካሂዱት ከጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከብሄራዊ መረጃ ደህንነት የተውጣጡ ሙያተኞች እንደሆኑ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ማንኛውም የውጭ አገር ገንዘብ የመመንዘር ኃላፊነት ያለው ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ውክልና የተሰጣቸው ባንኮች ብቻ እንደሆኑ በባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 ተደንግጓል።

አዋጁን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ ከ10 እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ሕግ ያዛል።

ይሁን እንጂ ወንጀለኞች በቁጥጥር ስር ሲውሉ በሕዝብና በመንግስት ላይ ካደረሱት ጉዳት አንጻር ቅጣቱ ዝቅተኛ ነው።

ይህንንም ከምግት ውስጥ በማስገባት ጥናቱ የወንጀሉን ግዝፈትና እየተወሰደ ያለውን ህጋዊ እርምጃ በሚመለከት መታየት ያለበትን ማስተካከያም ይዳሰሳል ነው ያሉት።

በተጨማሪም በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ የመጠቀም ተግባር እየተስፋፋ በመሆኑ ይህንን ተከትሎ ወንጀለኞችን ተጠያቂ በማድረግ ረገድ በተግባር ላይ ካለው ሕግ ጋር በማነጻጸር እየተወሰደ ያለው እርምጃ አስተማሪ አለመሆኑም እንዲሁ ይታያል።

በጥናቱ አገር አቀፍ ደረጃ ህገ-ወጥ የሰዎችና የጦር መሳሪያ ዝውውር ችግርንም እንደሚመለከት አስታውቀዋል።

የመረጃ አሰባሰብ ሂደቱ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የተከተለ አለመሆኑንና በዚህም የጥናቱን ውጤት በቅርቡ ይፋ ለማድረግ እንደሚያዳግት ተናግረዋል።

ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር መበራከቱንና ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባሩም መጠናከሩን የገለጸው ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ነው።

የኢትዮጵያን ብር ጨምሮ የተለያዩ አገራት ገንዘቦች በሕገ-ወጥ መንገድ እየተዘዋወሩ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።

በኮሚሽኑ የወንጀል መከላከል ዘርፍ የፈጥኖ ደራሽ ዳይሬክተር ኮማንደር አይሳ ዳመና ለኢዜአ እንደገለጹት በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ የሚሳተፉ ተጠርጣሪዎችን በመያዝ ለህግ የማቅረብ ተግባሩ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ወንጀለኞቹ ከሚያዘዋውሩት ገንዘብ ጋር እየተያዙ መሆኑንና የገንዘቡ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሕብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር በጋራ በመስራት ወንጀለኛው ከነገንዘቡ እንዲያዝ የሚያደርገው ጥቆማ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድም እንዲሁ

በፌዴራል ፖሊስ ብቻ በአራት ወራት ከ71 ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ብር፣ ከስድስት ሺህ በላይ ዩሮ፣ ከ36 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር እንዲሁም 204 ሺህ የደቡብ ሱዳን እና 21 ሺህ የሱዳን ፓውንድ መያዛቸውን አረጋግጠዋል።

ከፌዴራል ፖሊስ በተጨማሪ የጉምሩክ፣ የክልል የጸጥታ አካላትና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በየበኩላቸው ድርጊቱን የመቆጣጠር ስራ ያከናውናሉ።

የባለድርሻ አካላት ተሳትፎም ወንጀለኞችንም ሆነ ገንዘቡን በቁጥጥር ስር ለማዋል ማገዙን ተናግረዋል።

የገንዘብ ዝውውሩ ከሚደረግባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች መካከል ጅግጅጋ፣ ቶጎ ጫሌ፣ ሰመራ፣ ሞያሌ፣ ሚዛን ቴፒና መተማን ጠቅሰው በቤንሻንጉል ጉሙዝና በጋምቤላ ክልሎችም እንዲሁ በብዛት ይዘዋወራል ብለዋል።

የኮንትሮባንድ ንግድን ጨምሮ በህገ-ወጥ መንገድ ያፈሩትን ሃብት ለማሸሽና ከተጠያቂነት ለመዳን የሚደረግ ጥረት የገንዘብ ዝውውሩ ዋነኛ ምንጭ መሆኑንም አክለዋል።

ከኢትዮጵያዊያን በተጨማሪ የውጭ አገር ዜጎችም በህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውሩ እንደሚሳተፉና ናይጄሪያዊያን፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳናዊያን ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ ኮማንደሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም