ቀጥታ፡

በፕላዝማና በኮምፒዩተር የታገዘ ትምህርት እያገኘን አይደለም...ተማሪዎች

ሰቆጣ ታህሳስ 25/2011 በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ምክንያት በፕላዝማና በኮምፒዩተር የታገዘ ትምህርት እያገኘን አይደለም ሲሉ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የደሃናን ወረዳ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ።

በወረዳው የሲልዳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ ደበሳው ገናን ለኢዜአ እንደገለጸው በትምህርት ቤታቸው የመብራት አገልግሎት ባለመኖሩ ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ በፕላዝማ እና በኮፒውተር የታገዘ ትምህርት እያገኙ አይደለም፡፡

" የሲልዳ ቀበሌ እና አካባቢው ነዋሪዎች የመብራት ተጠቃሚ ባንሆንም ካለፈው ዓመት ጀምሮ የትምህርት ቤቱ ጀኔሬተር በመበላሸቱ የፕላዝማ ትምህርት እስካሁን ድረስ እያገኘን አይደለም " ብሏል፡፡

ትምህርቱን አለማግኘታቸው በዘንድሮው ዓመት ለሚወስዱት ሀገር አቀፍ ፈተና ከሌሎች ተማሪዎች ጋር እኩል ለመወዳደር እንቅፋት እንደሚሆንባቸው ስጋቱን ገልጿል።

በአሁኑ ወቅት ለፈተናው በክፍል ውስጥ መምህራን በሚሰጣቸው ትምህርት ብቻ እየተዘጋጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡

"በመብራት አቅርቦት ችግር ምክንያት ካለፈው ዓመት ጀምሮ በፕላዝማ ቴሌቪዥንና በኮፒውተር የታገዘ ትምህርት እያገኘን አይደለም" ያለቸው ደግሞ በቆውዝባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ተማሪ አበበች አሰፋ ናት፡፡

" የፕላዝማ ቴሌቪዥን በመማሪያ ክፍሉ ውስጥ ቢተከልም አገልግሎት በለመስጠቱ በትምህርታችን እየተጎዳን ነው" ብላለች ፡፡

የሲልዳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አለሙ ፀጋየ በትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የፕላዝማ እና የኮምፒውተር የተግባር ትምህርት እያገኙ እንዳልሆነ አምነዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነውን የፕላዝማ ትምህርት በትምህርት ቤቱ ተደራሽ ባለመሆኑ በተማሪዎች ውጤታማነት ላይ እንቅፋት መፍጠሩን ተናግረዋል።

እንደ ርዕሰ መምህሩ ገለጻ በትምህርት ቤቱ 20 ኮምፒውተሮች እና 20 ፕላዝማ ቴሌቪዥኖች አገልግሎት ሳይሰጡ በተለያዩ ክፍሎች ተገጥመው ይገኛሉ፡፡

የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ምህረት ረታ በበኩላቸው በወረዳው ካሉት ስድስት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በአራቱ ትምህርት ቤቶች በፕላዝማ እና በኮምፒውተር የታገዘ ትምህርት እየተሰጠ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሲልዳ ትምህርት ቤት ጀኔሬተር ካለፈው ዓመት ጀምሮ እንዲጠገን በተደጋጋሚ ጊዜ ጥረት ቢደረግም መስራት እንዳልቻለ ኃላፊው አመልክተዋል፡፡

የቆውዝባ ከተማ የመብራት ተጠቃሚ ቢሆንም ትምህርት ቤቱ በትራንስፎርመር ችግር ምክንያት ሳያገኝ መቅረቱን አቶ ምህረት ጠቁመዋል፡፡

የአርቢት እና ጥላላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አዲስ በመሆናቸው ጀኔሬተር እንደተሟላላቸው የገለጹት ምክትል ኃላፊው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የፕላዝማ ትምህርት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል፡፡

የደሃናን ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገብሩ ቸኮለ በቀጣይ የሲልዳ ትምህርት ቤት ጀኔሬተርን በባለሙያ ታይቶ የማይሰራ ከሆነም አዲስ እንደሚገዛ አስታውቀዋል።

ለቆውዝባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚሆን ትራንስፎርመር ለማስገጠም 460 ሺህ ብር ከፍለው ወረፋ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአምደ ወርቅ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ኃላፊ አቶ ደምሴ ነጋሲ ለቆውዝባ ትምህርት ቤት ትራንስፈርመር ለማቅረብ ከወረዳው አስተዳደር ጋር ውል መውሰዳቸውን ጠቁመው ትራንስፈርመሩ እንዲቀርብ ለሚመለከተው ዲስትሪክት ማሳወቃቸውን አስረድተዋል፡፡

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ደሃናን ወረዳ ከ2 ሺህ 400 በላይ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም