ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን ለውጥ ቻይና ትደግፋለች - ዋን ዩ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን ለውጥ ቻይና ትደግፋለች - ዋን ዩ
አዲስ አበባ ታህሳስ25/2011 ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ቻይና እንደምትደግፍ የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋን ዩ ገለጹ።
ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ዛሬ ረፋዱ ላይ ከቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋን ዩ ጋር በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ተወያይተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋን ዩ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ "ቻይና የኢትዮጵያ የልማት ስትራቴጂክ አጋር ናት"።
ይህ የሁለትዮሽ ትብብርም ለበርካታ ዓመታት የቆየና ጠንካራ መሆኑን ገልጸው በቀጠይም ይበልጥ ለማጠናከር ጠቃሚ ምክክር ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ቻይናን በተመለከተ የምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጠንካራ መሆኑንም ጠቁመው ቻይናም በተመሳሳይ ለኢትዮጵያ ትልቅ ቦታ ትሰጣለች ብለዋል።
በኢትዮጵያ ለውጥ እየተካሄደ ቢሆንም ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት እንደማይለወጥ ቻይና በጽኑ እንደምታምንም አስረድተዋል።
እንዲያውም ቻይና በኢትዮጵያ እያካሄደች ላለው የተኃድሶ እንቅስቃሴ ድጋፍ እንደምታደርግ ነው ያረጋገጡት።
የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብም አዋጭና ስኬታማ የልማት ጎዳና ላይ ለመድረስ የሚያስችል ጥበብና ችሎታ እንዳላቸውም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ጎን ለጎንም አገራቱ ያሏቸውን ትብብር በማጎልበት በዓለም አቀፍ ደረጃም በባለብዙ ወገን ድርድሮች ላይ ትብብር እንዲኖራቸው ተወያይተናል ብለዋል ሚኒስትሩ።
ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴም በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ስትራቴጂክ አጋርነት ከፈጠረችባቸው ጥቂት አገሮች መካከል ቻይና ግንባር ቀደም መሆኗን ተናግረዋል።
አጋርነቱ በምጣኔ ኃብት ብቻ ሳይሆን በሌሎች መስኮች ላይም የተመሰረተ መሆኑን ገልጸው ውጤታማና ለወደፊቱም ሊጠናከር የሚገባው መሆኑን አስረድተዋል።
በተለይም በምጣኔ ኃብት ያለውን ፍሬያማ ግንኙነት ቻይና ለአፍሪካ ልማት በዘረጋችው ማዕቀፍ ውስጥ ለማስፋትና ተጠቃሚነቷን ለማጎልበት ትሰራለች ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሠላምና ደኅንነትን ጨምሮ በሌሎች አጀንዳዎች ላይም ከቻይና ጋር የትብብር አድማሷን ለመስፋት እንደምትሰራ ፕሬዚዳንቷ መናገራቸውን የፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የኮሙኒኬሽንና የፕሮቶኮል ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አሸብር ጌትነት ገልጸዋል።
በቀጣይ መጋቢትም በቻይና በሚካሄደው 'ዋን ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሼቲቭ' በተሰኘው መርኃ ግብር ላይ ኢትዮጵያ ትሳተፋለች ተብሎ ይጠበቃል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ400 በላይ የቻይና ኩባንያዎች በአራት ቢሊዮን ዶላር ወጪ የኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ተሰማርተዋል።
ከእነዚህም 105ቱ በሽርክና ከኢትዮጵያዊያን ጋር የሚካሄድ ሲሆን በዚህም በድምሩ ከ100 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል።
የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነትም 'ለደቡብ ደቡብ ስትራቴጂካዊ አጋርነት' ውጤታማ ማሳያ መሆኑን የመስኩ አጥኚዎች እንደሚመስክሩ መረጃዎች ያሳያሉ።
በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋን ዩ በቡርኪና ፋሶ፣ ጋምቢያና ሴኔጋልም ተመሳሳይ ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።