ቀጥታ፡

ፍርድ ቤቱ በኮሎኔል ሰጠኝ ካሕሳይ ላይ የክስ መመሰረቻ ስምንት ቀናትን ፈቀደ

አዲስ አበባ ታህሳስ 25/2011 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቃቤ ሕግ በኮሎኔል ሰጠኝ ካሕሳይ ላይ ክስ ለመመስረት የተጠየቀውን ስምንት ቀናት ፈቀደ።

ፖሊሲ ኮሎኔል ሰጠኝ ካሕሳይ ከተጠረጠሩበት ወንጀሎች ውስጥ ሁለቱን በምርመራ በማጠናቀቁ መዝገቡን ለአቃቤ ሕግ ማስረከቡን ገልጿል።

ኮሎኔል ሰጠኝ ካህሳይ በቁጥጥር ስር የዋሉት የዐቃቤ ህግ የምርመራ ሂደትን በማደናቀፍ ወይም ሰነድ በማስጠፋት ተጠርጥረው እንደነበር ይታወቃል።

በሒደት ግን ጉዳዩን የያዘው ፖሊስ አዲስ ግኝት ብሎ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው ተጠርጣሪው ላይ ተጨማሪ የሙስና ወንጀል በምርመራ እንደተገኝባቸው ተገልጿል።

ተጠርጣሪው ኮሎኔል ሰጠኝ ካሕሳይ የብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ኩባንያ በሆነው ሃይቴክ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ የሰው ሃብት አስተዳደር ሆነው በሚያገለግሉበት ወቅት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ትራንስፎርመር እንዲያቀርብ የግዥ ውል ተፈራርመዋል።

ነገር ግን ያለምንም ጨረታ ከወልዳይ ገብረማርያም ብቸኛ አስመጪ ከ85 ሚሊዮን 783 ብር በላይ ግዥ በመፈጸም በመንግስትና ህዝብ ሃብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል በሚል ፖሊስ በሙስና ወንጀል ጠርጥሯቸዋል።

ተጠርጣሪው ኮሎኔል ሰጠኝ 'ኮሞቹ አሙኔሽን ኢንጂነሪንግ' የተሰኘ ተቋም የሰው ሃብት ልማት ሃላፊ በነበሩበት ወቅትም ህጉን ያልተከተለ የ15 ሚሊዮን ብር ግዢም እንዲፈጸም አድርገዋል በሚል እንደተጠረጠሩም አስታውቋል።

በነዚህ ሁለት መዝገቦች ፖሊስ ምርመራዬን አጠናቅቄያለሁ በማለቱም መዝገቡን ለአቃቤ ሕግ ማስረከቡን ዛሬ ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊስ መዝገቦቹን እየከፋፈለ ለአቃቤ ሕግ መስጠቱ በውስጠ ታዋቂነት ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ እየጠየቀ መሆኑን የሚያመላክት ነው በማለት ተቃውመዋል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን ያደመጠው ፍርድ ቤቱ አቃቤ ሕግ የጠየቀውን የክስ መመስረቻ ስምንት ቀናት በመፍቀድ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም