ቀጥታ፡

የፕሪሚየር ሊጉ ዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ ይጀምራሉ

አዲስ አበባ ታህሳስ 25/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ነገ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጀምራል።

ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰዓት መከላከያ ከአዳማ ከተማ የሚጫወቱ ሲሆን በሀዋሳ ስታዲየም ደቡብ ፖሊስ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰአት የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ቡና ስሑል ሽረን ያስተናግዳል።

በክልል ከተሞች በድሬዳዋ ስታዲየም ድሬዳዋ ከተማ ከባህርዳር ከተማ፣ በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ደደቢት ከወላይታ ድቻ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ የሚጫወቱ ይሆናል።

እሁድ ታህሳስ 28 ቀን 2011 ዓ.ም የአዲግራት ስታዲየም እያሳደሰ የሚገኘው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከፋሲል ከተማ ጋር ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የአማራና የትግራይ ክልል እግር ኳስ ክለቦች ከአንድ ዓመት በኋላ በሜዳቸው የሚያደርጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ነው።

ጨዋታው የሚደረገው የአማራ እና የትግራይ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ ስፖርት ኮሚሽኖች፣ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች እና ክለቦች በየክልላቸው ችግሮችን መፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው ለጉዳዩ መፍትሔ መስጠታቸውን ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በማሳወቃቸው ጨዋታዎቹ እንዲከናወኑ ፌዴሬሽኑ መወሰኑን ተከትሎ ነው።

ሰኞ ታህሳስ 29 ቀን 2011 ዓ.ም በሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ሀዋሳ ከተማ ከጅማ አባ ጅፋር፣ በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከሲዳማ ቡና በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

በሌላ ዜና ዛሬ በሀዋሳ ስታዲየም በሲዳማ ቡናና ጅማ አባ ጅፋር መካከል በተካሄደው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በጨዋታው የሲዳማ ቡናው ዳግም ንጉሴ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና ነጥቡን ወደ 13 ከፍ በማድረግ በነበረበት ሶስተኛ ደረጃ የተቀመጠ ሲሆን ጅማ አባ ጅፋር ነጥቡን ወደ ስድስት ከፍ በማድረግ በነበረበት 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ ቡና በ15 ነጥብ ሲመራ፣ ሀዋሳ ከተማ በ14 ነጥብ ሁለተኛ፣ ሲዳማ ቡና በ13 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ስሑል ሽረ፣ ደቡብ ፖሊስና ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በስድስት ጎል ሲመራ፣የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ በአምስት የሀዋሳ ከተማዎቹ ታፈሰ ሰለሞንና እስራኤል እሸቱ እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለው በተመሳሳይ አራት ጎሎች ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም