ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማህበር መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው

አርባምንጭ ታህሳስ 25/2011 የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማህበር መደበኛ ጉባኤውን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እያካሄደ ነው፡፡

የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ዓባይ በላይሁን ማህበሩ በ1999 ዓ.ም ከተቋቋመ ወዲህ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራትና በስፖርት ዘርፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ሚና ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከእዚህ በተጨማሪ የእርስ በርስ ግንኙነትን ለማጠናከርና ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚያንጸባርቁ እሴቶችን ለማሳደግ ማህበሩ ትኩረት መስጠቱን ነው የገለጹት፡፡

አቶ አባይ አንዳሉት ባለፉት 3 ዓመታት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በተመሳሳይ ወቅት ማግኘት ባለመቻሉ በየዓመቱ ይዘጋጅ የነበረው የስፖርት ፌስቲቫል ተቋርጧል፡፡

ጉባኤው በአምስት ዓመት ስትራቴጂክና በ2011 ዓ.ም ዕቅድ ላይ ውይይት በማድረግ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል፡፡

በውጭ ኦዲተር የተከናወነው የፋይናንስ ክንውን ሪፖርትም ለጉባኤው ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

ጉባኤው የስፖርት ዘርፉን ለማዘመን አዲስ በተዘጋጀው የውድድር መመሪያና የስነ-ምግባር ደንብ ላይም ውይይት እንደሚያደርግ ተመልክቷል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽን፣ ስፖርት ኮሚሽን እንዲሁም የ40 ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች መገኘታቸው ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም