ወጣቱ አገራዊ ለውጡን አጠናክሮ ሊያስቀጥል ይገባል....የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ አገራዊ ለውጡን አጠናክሮ ሊያስቀጥል ይገባል....የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ
ባህርዳር ታህሳስ 25/2011 ወጣቱ ከስሜታዊነት በመራቅና ምክንያታዊ በመሆን በመስዋዕትነት የመጣውን አገራዊ ለውጥ አጠናክሮ ሊያስቀጥል እንደሚገባ የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽፈት ቤት ኃላፊ ገለጹ።
የአማራ ዴሞክራሲአዊ ፓርቲ (አዴፓ) ወጣቶች ሊግ 4ኛ መደበኛ ጉበኤ “የወጣቶች የነቃ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለአገራዊ አንድነትና ቀጣይነት ላለው ለውጥ “ በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተጀምሯል።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ምግባሩ ከበደ በሊጉ ጉባኤ መክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ እንዳሉት አገሪቱ አሁን በተስፋና በውጥረት ውስጥ ትገኛለች።
ወጣቱ የሕይወት እና የአካል መስዋትነት ከፍሎ ያመጣውን ለውጥ ጥቅማቸውን የተነካባቸው ኃይሎች ለማደናቀፍ እየሰሩ በመሆናቸው ወጣቱ በሰከነ መንገድ እንዲከታተላቸው አመልክተዋል።
የአማራ ወጣት ከሌሎች የኢትዮጵያ ወጣቶች ጋር ሆነው በመስዋዕትነት ጭምር የመጣውን አገራዊ ለውጥ በስሜት ፖለቲካ ሳይሆን ምክንያታዊ በመሆን አጠናክሮ ሊያስቀጥለው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
"በአገሪቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ አፍሪካንና ሌላውን ዓለም ያነጋገረ ለውጥ ቢመጣም አሁንም ለውጡን ለመቀልበስ የሚፈልገው ቡድን ሴራውን ለማሳካት ሌት ተቀን እየሰራ ነው" ብለዋል።
"ሴራውን ለመመከት የለውጡ ጠንሳሽ ከሆነው ወጣት የተሻለ ሌላ ኃይል የለም" ያሉት አቶ ምግባሩ፣ የአማራ ወጣቶች እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከሌሎች የሀገሪቱ ወጣቶች ጋር በመሆን ለውጡን ለማስቀጠል እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ክልሉ የስርአት አልበኞች መናኽሪያ የሆነ ለማስመሰል ሆን ተብሎ እየተሰራ በመሆኑ በክልሉ ውስጥ ያሉ የጸረ-ለውጥ ግብረ አበሮችና ተባባሪዎችን ወጣቱ በመለየት ለህግ ሊያቀርባቸው እንደሚገባም አመልክተዋል።
ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ የተዘራው የጥላቻ ፖለቲካ የአማራ ወጣቶች ተደራጅተው ለክልላቸውም ሆነ ለአገሪቱ የበኩላቸውን ድርሻ በአግባቡ እንዳይወጡ ሲያደረግ መቆየቱን የተናገረው ደግሞ የአዴፓ ወጣቶች ሊግ ሊቀመንበር ወጣት ሙቀት ታረቀኝ ነው።
"የአማራ ወጣት እንደአባቶቹ ሁሉ በኢትዮጵያ ሉአላዊነት ላይ አይደራደርም" ያለው ወጣት ሙቀት፣ አሁን ለተገኘው አገራዊ ለውጥ የአማራ ክልል ወጣት ከሌሎች የአገሪቱ ወጣቶች ጋር በመሆን የጎላ ድርሻ ማበርከቱን ተናግሯል።
ይሁን እንጂ አሁንም አማራው ክሌሎች ብሔሮች ጋር እንዲጋጭ ይደረግ የነበረውን ሴራ በማስቀጠል ለውጡ እንዲደናቀፍ እየተሰራ መሆኑን ጠቁሞ የአማራ ወጣት ከመቼውም ጊዜ በላይ ለውጡን ለማስቀጠል እንዲንቀሳቀስ ጥሪ አቅርቧል።
"በአማራው ላይ ባለፉት ዓመታት ሲደርስ የነበረው የሞራልና የሰብአዊ መብት ጥሰት ዳግሞ እንዳይከሰት ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ጋር በመሆን ያለመታከት እንሰራለን" ብሏል።
ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀን በሚቆየው ጉባኤው ላይ የክልሉ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የእህትና የአጋር ድርጅቶች ወጣት ሊግ አመራሮችና በርካታ የክልሉ ወጣቶች በመሳተፍ ላይ መሆናቸው ታውቋል።