የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም የለንም-የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ - ኢዜአ አማርኛ
የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም የለንም-የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ

አዲስ አበባ ታህሳስ 25/2011የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም እንደሌለው የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት ሞታ ለኢዜአ እንደገለጹት የኤጀንሲው የሰው ኃይል፣ ተሽከርካሪና ሌሎች ግብዓቶች አቅም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አይደለም።
ኤጀንሲው የሰው ኃይሉን ለማጠናከር የአደረጃጀት ማሻሻያና የመዋቅር ጥናት ተከናውኗል፤ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይጸድቃል ተብሎም ይጠበቃል።
የተማሪዎችን መረጃ ከኤጀንሲው ጋር የሚያስተሳስርና በኢንፎርሜሽን ቴክኖለጂ የታገዘ የመረጃ ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸው፤ ይህም ተቋማት ላይ የሚደረገውን ክትትል ያግዛል ብለዋል።
እንደ አቶ ታምራት ገለጻ የኤጀንሲው የአቅም ውስንነት የግል ተቋማት መመሪያዎችን ጠብቀው እየሰሩ ስለመሆናቸው በቁጥጥር ሳይሆን በኮሌጆቹ የሙያዊ ኃላፊነትና ስነ ምግባር ላይ እንዲወሰን አድርጓል ።
ሆኖም አብዛኛዎቹ በተሰጣቸው ኃላፊነት መሰረት እየሰሩ አለመሆኑን ከሕብረተሰቡ የሚደርሱ ጥቆማዎችና ኤጀንሲው የሚያደርገው ቁጥጥር ያመለክታል ብለዋል።
ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ መስፈርቶች ውጭ ተማሪዎችን መቀበል፣ ዕውቅና ሳይኖራቸውና ሳያሳድሱ መቀበልና ማስተማር፣ ዕውቅና ባልተሰጣቸው የትምህርት ክፍሎች ተማሪዎችን መቀበልና ማስተማር፣ የትምህርት ግብዓቶችን ሳያሟሉ ማስተማርና ሌሎች ክፍተቶችም መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ባለፉት ዓመታት በተለይም ከ2009 ዓ.ም በፊት ኤጀንሲው በአግባቡ መቆጣጠር ባለመቻሉ ሳቢያ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ መስፈርቶች ውጭ ተማሪዎችን ተቀብለው ያስተማሩና አስመርቀውም ወደ ስራ ያሰማሩ በርካቶች መኖራቸውንም አንስተዋል።
ከመመሪያ ውጭ በመስራታቸው ሙሉ ለሙሉ እንዲዘጉ የተደረጉና በከፊል የተዘጉ ያሉ ሲሆን፤ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታዩ ያሉ የግል ተቋማት መኖራቸውንም አንስተዋል።
በአዲስ አበባ ሴንትራል የጤና ኮሌጅና ሜድኮ ባዮ ሜዲካል ኮሌጅ፣ በመቀሌ ናይል ኮሌጅ፣ በድሬዳዋ ኢ አር ቲ ኮሌጅ ሙሉ በሙሉ ከተዘጉ መካከል ተጠቅሰዋል።
የአልፋ ዩንቨርስቲ፣ ሳንቴ ሜዲካል ኮሌጅ፣ ሰሚት ኮሌጅና ጅግዳን ኮሌጅ ደግሞ ከተፈቀደላቸው የትምህርት ክፍል ውጭ በማሰተማራቸው በከፊል እንዲዘጉ መደረጉንም አክለዋል።
በመሆኑም ተማሪዎች ፣ ወላጆች ፣ ቀጣሪ ድርጅቶችና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ስለ ተቋማት ዕውቅናና ፍቃድ ዕድሳት በአግባቡ በማጣራት ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
ሕብረተሰቡ የግል ተቋማት ህገ ወጥ ድርጊት ላይ መረጃ በሚያገኝበት ወቅት የትምህርት ጥራትን ጉዳይ የአገር ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ለኤጀንሲው ጥቆማ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል መመሪያ በመጣስ በህግ የሚጠየቁ የትምህርት ተቋማትን ለህግ ለማቅረብ የፍትህና አስተዳደር አካላት ኃላፊነታቸውን ያለመወጣትና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር በመኖሩ ብዙ ፈተና እንደሚያጋጥማቸውም ተናግረዋል።
የትምህርት ጥራት ማስጠበቅ የአገር ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ዳይረክተሩ ጥራቱን ለማስጠበቅ በጋራ ካልተሰራ ውጤት ማስመዝገብ ስለማይቻል የሁሉም አካል ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማስፋፊያ ስራ በስፋት መሰራቱንና የግል ተቋማትም ቁጥር በከፍተኛ መጠን ማደጉን ይናገራሉ።
ሆኖም ኤጀንሲው በአገር አቀፍ ደረጃ እነዚህን ተቋማትን የመከታተል፣ የመደገፍና የመቆጣጣር ኃላፊነቱን ለመወጣት በሚያስችለው መልኩ የሰው ኃይልና ሌሎች ግብዓቶችን የማሟላት ስራ አልተሰራም ብለዋል።
ቀደም ሲል የኤጀንሲው የደሞዝ ደረጃ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ተመጣጣኝ እንደነበር ገልጸው በቅርብ አመታት ውስጥ ተቋማቱ የደሞዝ ማሻሻያ ተግባራዊ ባደረጉበት ልክ የኤጀንሲው ደሞዝ ማሻሻያ ያለመደረጉም ክፍተት መሆኑን ዶክተር ሳሙኤል ገልጸዋል ።
ይህንንም ለማስተካከል የተዘጋጀው የሰው ኃይል መዋቅር ጥናት ሂደት ላይ መሆኑንና የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ይህንን ተከታትሎ የማሰፈጸም ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የኤጀንሲውን ስራዎች ስፋት ማዕከል ያደረገ በጀት እንዲመደብ ለመደገፍም በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት።
የተሽከርካሪ ግብዓትም ከስራው ስፋት አንጻር ባይሆንም ካለው የመንግስት ውስን ሀብት ላይ ትኩረት ተሰጥቶበት እንዲሰጣቸው ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል ።