በሰሜን ሸዋ ዞን የ118 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታ ሥራ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ሸዋ ዞን የ118 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታ ሥራ ተጀመረ
ደብረ ብርሃን ታህሳስ 25/2011 በሰሜን ሸዋ ዞን ከጣርማ በር መለያ፣ ሰፌድ ሜዳና ሞላሌ ወገሬ የ118 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ግንባታ ሥራ ተጀመረ።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዳይሬክተር ኢንጀነር ሃብታሙ ተገኝ መንገዱ የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን አካል መሆኑንና በ3 ዓመት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።
የኮንክሪት አስፓልት መንገዱ ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የሚደረግበት ሲሆን ግንባታው የሚከናወነውም በመከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅት መሆኑን አመልክተዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ መንገዱ በከተማ 19 ሜትር፤ በገጠር ደግሞ ከ7 እስከ 10 ሜትር ስፋት ይኖረዋል።
መንገዱ የመዘዞ፣ የመለያ፣ የማሃል ሜዳና የሞላሌ ወገሬ አነስተኛ ከተሞችን ከማገናኘቱም ባለፈ ቀዎት፣ ግሸን፣ መንዝ ጌራ እና መንዝ ቀያ ያሉ አጎራባች ወረዳዎችን እርስ በእርስ ያስተሳስራል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድምአገኘሁ በበኩላቸው "የመንገዱ መገንባት የህብረተሰቡን የመንገድ ይገባልኝ ጥያቄ ለመመለስ ያስችላል" ብለዋል።
የመንገዱ መገንባትም በአካባቢው በሚገኙ አምስት ወረዳዎች የሚመረቱ የተለያዩ የግብርና ምርቶችንና የቁም እንስሳትን ወደመሀል ገበያ በማቅረብ አርሶ አደሩን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
የትራንስፖርት ሚኒስቴሯወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት መንገዱ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አስታውቀዋል።
"በሃገሪቱ የመንገድ አውታሮችን ለማስፋት መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው" ያሉት ሚኒስትሯ ይህም ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ለማሸነፍ እየተደረገ ላለው ጥረት የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
መንገዱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ጥራቱን ጠብቆ እንዲከናወን በመንግስት በኩል ተገቢ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ አመልክተው የአካባቢው ማህበረሰብም ለመንገዱ ግንባታ ተባባሪ በመሆን የድርሻቸውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
የመካላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ አቶ ፍሰሃ ወልደሰንበት በበኩላቸው ግንባታው ጥራቱን ጠብቆ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ለአገልግሎት እንዲበቃ ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ አመልክተዋል።
የመንገዱን ግንባታ ለማስጀመር በተዘጋጀ ስነስርዓት ላይ ከፌደራልና ከክልል የተውጣጡ አመራሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በተመሳሳይ በነገው እለትም ከ1 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የደብረ ብርሃን አንኮበር 42 ኪሎ ሜትር የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ሥራ በይፋ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።