ለውጡ ከቻይና ጋር ያለንን ግንኙነት ይበልጥ ያጠናክረዋል-ዶክተር ወርቅነህ - ኢዜአ አማርኛ
ለውጡ ከቻይና ጋር ያለንን ግንኙነት ይበልጥ ያጠናክረዋል-ዶክተር ወርቅነህ
አዲስ አበባ ታህሳስ 25/2011 የኢትዮጵያ ለውጥ ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተናገሩ።
ዶክተር ወርቅነህ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ካሉት የቻይና አቻቸው ዋንግ ዪ ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ከውይይቱ በኋላ በሰጡት የጋራ መግለጫ ዶክተር ወርቅነህ እንዳሉት የኢትዮጵያና ቻይና ግንኙነት በሁለቱ አገራት የጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ነው።
በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የኢኮኖሚና ፖለቲካ ግንኙነት እያደገ መምጣቱን በማውሳት ባለፉት ዓመታት ቻይና በኢትዮጵያ ዕድገት በጎ ተጽዕኖ ፈጥራለች ብለዋል።
አሁን በኢትዮጵያ ያለው ለውጥም ከቻይና ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ ያጠናክረዋል ነው ያሉት።
ሁለቱ አገሮች በአፍሪካ በጋራ የሚሰሯቸው ጉዳዮች መኖራቸውን በመግለጽ "ቻይና የኢትዮጵያ ስትራቴጂክ አጋር መሆኗ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በበኩላቸው ቻይናና ኢትዮጵያ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በቻይና አፍሪካ ግንኙነት ኢትዮጵያን ወደፊት ለማምጣት እንደሚሰራ ነው የተናገሩት።
በመሰረተ ልማት፣ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ግብርና፣ ሃይል ማመንጫና የሰው ሃብት ልማት ላይ በትብበር ለመስራት በውይይታቸው መስማማታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን በማሳደግ ለህዝቦቿ የተሻለ ህይወት ለመፍጠር በምታደርገው ጥረት ቻይና ድጋፏን እንደምትቀጥል ዋንግ ዪ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲመጣ ያደረገችውን ጥረት ቻይና እንደምታደንቅ ገልጸው በቀጣይ በሰላምና ጸጥታ ጉዳይ አብረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ቻይና በኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ጉዳዮች አብረው እንደሚሰሩ በውይይታቸው ማንሳታቸውንም ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሰጡት የጋራ መግለጫ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።
በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ለማድረግ በትናንትናው ዕለት አዲስ አበባ የገቡት የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቆይታቸው ከተለያዩ የመንግስት ኃላፊዎች ጋር ይወያያሉ ተብሏል።
የኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በ1970ዎቹ የተጀመረ ሲሆን አገራቱ በኢንቨስትመንት፣ ንግድ፣ መሰረተ-ልማትና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ የተጠናከረ ግንኙነት አላቸው።