በምስራቅ አማራ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን መርሃ ግብርን ለማስፈጸም ችግር እያጋጠመ መሆኑ ተጠቆመ

ደሴ ታህሳስ 25/2011 በምስራቅ አማራ የጤና መድህን አባላት በጤና ተቋም የመገልግል ልምድ በማደጉ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን መርሃ ግብሩን በአግባቡ ለማስፈጸም መቸገራቸውን የተለያዩ ወረዳ አመራሮች ገለጹ። 

በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብደላ ሸህ አህመድ እንዳሉት በወረዳው በማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ አባላት አገልግሎቱን የመጠቀም ባህላቸው እያደገ ነው።

ከእዚህ በተጨማሪ ለህክምና በአጭር ጊዜ ውስጥ ደጋግመው መምጣታቸው ጤና ተቋማቱ ከተሰባሰበው ገንዘብ በላይ አገልግሎት እንዲሰጡ እያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያትበዞኑ የሚገኙ የጤና ተቋማት በበጀት ዓመቱ እስካሁን ድረስ ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንደደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡

የዞኑ አስተዳደር ከ600 ሺህ ብር በላይ ድጎማ ቢያደርግም ችግሩን ማቃለል እንዳልተቻለ ዋና አስተዳዳሪው አመልክተዋል፡፡

በደረሰው የገንዘብ ኪሳራ ምክንያት መድኃኒቶችን ማሟላት ባለመቻሉም የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መድኃኒቶችን ከግለሰብ መድኃኒት ቤቶች በውድ ዋጋ ለመግዛት እየተገደዱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን የመቄት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይማኖት ጋሹ በበኩላቸው ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን በወረዳው በህብረተሰቡ ዘንድ  ተቀባይነት እያገኘ ቢመጣም ጤና ተቋማቱ በግብአት የተደራጁ ባለመሆናቸው የሚጠበቀውን አገለግሎት መስጠት እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

ጤና ተቋማቱ የአልትራሳውንድ፣ ኤክስሬይ ማሽንና ሌሎች ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎች ስሌሏቸው በአባልነት የተመዘገቡ ተጠቃሚዎች አገልግሎቱን የሚያገኙት ከግለሰብ ጤና ተቋማት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን የተሁለደሬ ወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከድር አህመድ በበኩላቸው በተያዘው ዓመት ብቻ ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ በወረዳው ላይ መድረሱን አስታውሰዋል፡፡

ወረዳው ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ድጎማ ቢያደርግም መርሃ ግብሩን በሚፈለገው ደረጃ ማስቀጠል ባለመቻሉ የክልሉ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የፈውስ ህክምናና ተሃድሶ አገልግሎት ዋና ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አበበ ዳኘው በክልሉ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ከተገበሩ 156 ወረዳዎች 22ቱ ወጪያቸውን መሸፈን እንዳቃታቸው አስታውቀዋል፡፡

በአገልግሎቱ የተገኘውን ሃብት የማስተዳደር አቅም ውስንነት፣ የአባላት ቁጥርን ማሳደግ አለመቻል፣ የአደረጃጀትና መሰል ችግሮች ጤና ተቋማቱ ገቢያቸውን እንዳያሳድጉ እንዳደረጋቸው አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ በራሱ ከሚያደርገው ድጋፍና ክትትል ባለፈ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከሚደጉመው በጀት ኪሳራ ላይ ለወደቁ ጤና ተቋማት ድጋፍ እንደሚደረግም አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አበባው ገበያው በበኩላቸው የግብዓትና የአደረጃጀት ችግርን ለመፍታት የሆስፒታሎችን ደረጃ የማሳደግ ሥራ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው የአማራ ክልል በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ሽፋን በአገር አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዘርፉ እየታዩ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ርዕሰ መስተዳደሩ ተናግረዋል፡፡

በምስራቅ አማራ ከሚገኙ ዞኖችና ወረዳዎች የተውጣጡ ከ200 በላይ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የማህበረሰብ ጤና መድህን ሽፋንን አስመልክቶ ትናንት በደሴ ከተማ በተካሄደ ውይይት ላይ ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም