ፍርድ ቤቱ በአቶ አብዲ ሙሃመድ ኡመር ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

72

አዲስ አበባ ታህሳስ 25/2011 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት  በቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ሙሃመድ ዑመር ላይ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው 4ኛ ወንጀል ችሎት በቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ሙሃመድ ዑመርና ከእሳቸው ጋር በመተባበር በተጠረጠሩት ሶስት ተከሳሾች ላይ ነው ፖሊስ ሲያካሒድ የነበረውን የምርመራ ውጤት ያደመጠው፡፡

ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው የምርመራ ጊዜ የ15 ሰዎች ምስክርነት ቃል መቀበሉንና በጅግጅጋ ከተማና ሌሎች አካባቢዎች የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ የቪዲዮና የምስል መልዕክቶችን የማስተረጎም ስራ ሲሰራ መቆየቱን አስረድቷል

በቀጣይም "ተጨማሪ የተጎጂ ቤተሰቦችን የምስክርነት ቃል መቀበል፣ በጅምላ የተገደሉና የተቀበሩ ሰዎችን አስከሬን ምርመራ ውጤት ማምጣትና በወንጀሉ የተሳተፉ ግብረ አበሮችን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ ይቀረኛል" በሚል ነው  የምርመራ ጊዜውን የጠየቀው።

የተጠርጣሪ ተከላካይ ጠበቆች በበኩላቸው ''ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ 4 ወር ከ10 ቀን በመሆኑ ፖሊስ በተደጋጋሚ የሚጠይቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በፍጥነት ፍትሕ የማግኝትን ሕገ መንግስታዊ መብታቸው ላይ ጫና እንደሚያሳድር'' ገልጸዋል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን ያደመጠው ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ከቦታው ርቀት አንፃር እያካሔደ ያለው የምርመራ ስራ ውስብስብ መሆኑን በመግለጹና ይሕንንም ከግምት በማስገባት ስራውን ለማጠናቀቅ የጠየቀውን የ14ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል። በዚህ መሰረትም ለጥር 10 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም