ባለሃብቶች ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ከመንግስት ጋር ተቀናጅተው መስራት እንዳለበቸው ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
ባለሃብቶች ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ከመንግስት ጋር ተቀናጅተው መስራት እንዳለበቸው ተመለከተ
ፍቼ ታህሳስ 24/2011 ባለሀብቶች የህዝባቸውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከመንግስት ጋር ተናበው መስራት እንዳለባቸው ተመለከተ፡፡
በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን የመንግስትና የባለሀብቶች የጋራ ፎረም በፍቼ ከተማ ዛሬ ተካሂዷል፡፡
በዚህ ወቅት የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ ጠሃ እንደገለፁት የክልሉ ባለሀብቶች በኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለህዝባቸው ተጠቃሚነት ጭምር ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ።
በእስካሁኑ ተሞክሮ ለባለሀብቱ በርካታ የመሰረተ ልማትን ጨምሮ ልዩ ልዩ ማበረታቻዎች ቢደረጉም ባለሃብቶች ግን በሚፈለገው መጠን ለህዝባቸው ተጠቃሚነት ትኩረት እንዳልሰጡ ተናግረዋል ።
ጥቂት የማይባሉ ባለሀብቶች በተረከቡት መሬት ወደ ሥራ አለመግባት፣ በኢንቨስትመንት ሰበብ በወሰዱት ብድርና ማበረታቻ ከዓላማ ውጪ ለገንዘብ ትርፍ ብቻ መንቀሳቀስ ጐልተው የሚታዩ ችግሮች ናቸው፡፡
በዚህም ምክንያት ከመስኩ ብዙሀኑ ተጠቃሚ ማድረግ እንዳልተቻለ አስረድተዋል ።
ይህንን ችግር በዘላቂነት ለማስወገድ ኮሚሽኑ የለውጥ ሂደትን ተከትሎ የህግ፣ የአደረጃጀትና የመመሪያ ማሻሻያ በማድረግ ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በተለይ የየአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ በማጥናትና በመለየት በክላስተር መሰማራት የሚቻልበት ሁኔታ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶት ተፈፃሚ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡
የፎረሙ ዓላማ በክልሉና በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶች የአስተዳደር፣ የአገልግሎት፣ የአቅርቦትና የልዩ ፍላጐት ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አስቴር ዘውዴ ናቸው፡፡
በፎረሙ የተገኙ አንዳንድ ባለሀብቶች ከመንግስት፣ ከህዝብና ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥብቅ ትስስር በመፍጠር ፀጥታን ጨምሮ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
ከባለሀብቶቹ መካከል በሸኖ ከተማ በአግሮ ኢንዱስትሪ ሥራ የተሰማራው የአላስካ ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ለማወርቅ አብርሃም በፀጥታ ችግሮች ጭምር ከመንግስትና ከህዝብ ጋር ተባብረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
በተለይ ከውጭ ያመጧቸው የወተት ማቀነባበሪያ መሳሪያዎች ወደ ሥራ ለማስገባት የገጠማቸውን የኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከሌሎች ባለሀብቶችና ከመንግስት ጋር ተናቦ በፈረቃ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በውጫሌ ወረዳ በሲሚንቶና ኖራ ማምረት የተሰማራው የጀማ ፒኤልሲ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ኤልሳቤት ወልዱ በበኩላቸው ፋብሪካቸው በኤሌትሪክ ኃይል እጥረት ምክንያት የማምረት አቅሙን ከግማሽ በታች እንዳወረደ ተናግረዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት ግን ከመንግስትና ከህዝብ ጋር ተቀራርቦ በመስራት ማጣጣም እንደሚቻል ገልጸው በተለይ ሌሎች የኃይል አማራጮችን ለማቅረብ የመንግስት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ፋብሪካቸው በአካባቢው የሚታዩ ማህበራዊ ችግሮች እንዲቃለሉ የድርሻውን ለመወጣት እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡