ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ዘላቂ ሠላምና ደኅንነት ርብርብ አድርጋለች - አምባሳደር ታዬ

አዲስ አበባ ታህሳስ 24/2011 ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የተለዋጭ አባልነት ቆይታዋ ለምስራቅ አፍሪካ ዘላቂ ሠላምና ደኅንነት ርብርብ አድርጋለች ተባለ።

በመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ አምባሳደር ታዬ አስቀሥላሴ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ ቆይታዋ ውጤታማ ሥራ መስራቷን አረጋግጠዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር እርቅ ማውረዷን ተከትሎ ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ እንዲነሳ አገራትን በማስተባበር ወሳኝ ሚና መጫወቷን ገልጸዋል።

ለዚህም ከሌሎች የምክር ቤቱ ቋሚ አባላት ጋር በመቀናጀት የተሰራ ሥራ መሆኑን ገልጸው ግጭት ለሚስተዋልበት ለአፍሪካ ቀንድ ትልቅ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።

በአቢዬ ግዛት የተሰማራው የመንግስታቱ ድርጅት የሠላም አስከባሪ ሠራዊት ውጤታማ ሥራ እንዲሰራ በኢትዮጵያ ሠራዊቱን እንዲመራና በዚህም ላይ አገራት ይሁንታ ቸረዋታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ተወካዮች ጋር በመተባበር በአቢዬ የተሰማራው የመንግስታቱ ድርጅት ሠራዊት የቆይታ ጊዜ እንዲራዘም ማድረጓን በእምርታ አንስተውታል።

በሱዳን ዳርፉር የተሰማራው የሠላም አስከባሪ ሠራዊትም ውጤታማ ሥራ እንዲሰራና አገሪቷ አንድትረጋጋ ጠቃሚ ምክረ ኃሳብ በማቅረብም ጭምር ማገዟን ጠቁመዋል።

በሶማሊያም ማዕከላዊ መንግሥት እንዲጠናከር ለማስቻል የአፍሪካ ኅብረት የሠላም አስከባሪ ሠራዊት (አሚሶም) ከመንግስታቱ ድርጅት ሙሉ ድጋፍ እንዲያገኝ ተሰርቷል ነው ያሉት።

በብሩንዲ፣ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዘላቂ መረጋጋት ለማስፈን ድምጽ ከማሰማት ባለፈ ኢትዮጵያ የውሳኔ ሀሳብ ማቅረቧንም ጠቅሰዋል። 

በሌላ በኩል በየመንና በሶሪያ ግጭትን ተንተርሶ በሚቀሰቀሱ የሰብዓዊ ቀውሶች አፈጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ የመቀስቀስ ሥራም መሥራቷን አስረድተዋል። 

የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅና ገጽታዋን በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ለማስተዋወቅ በተከናወኑት ተግባራትም ኢትዮጵያ ቆይታዋን በአግባቡ መጠቀሟን አብራርተዋል።

አሁን ላይ ትኩረት የተሰጠው የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተም ኢትዮጵያ ለመፍትሄው አዎንታዊ ሚና መጫወቷን ተናግረዋል። 

በሁለት ዓመት ቆይታዋ ውስጥ በምክር ቤቱ በተካሄዱ 560 ሰብሰባዎችና 109 የወሳኔ ኃሳቦች ላይ ኢትዮጵያ ተሳትፎ ማድረጓን አምባሳደር ታዬ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም