በሀገሪቱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን 90 በመቶ መቀነስ ተችሏል ---የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር

አዳማ ታህሳስ 24/2011 በሀገሪቱ በሴቶች አካል ፣ አእምሮና ስነ ልቦና ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ የሚያሳድሩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች 90 በመቶ መቀነስ መቻሉን የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የተካሄዱ ሀገራዊ ንቅናቄዎች ያመጡትን ለውጦችና የተገኙ ውጤቶችን የሚገመግም የሁለት ቀናት መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

የሴቶች ፣ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ የአለም ፀጋይ አስፋው እንደገለጹት በህብረተሰቡ ውስጥ የነበሩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሴቶች አካል፣አእምሮና ስነ ልቦናዊ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ የፈጠሩ ኋላቀር ተግባራት ናቸው ።

ለመከላከልና ድርጊቱን ለማስቀረት  ባለፉት ዓመታት  በተደረጉት ጥረቶች ከማህበረሰቡ የአስተሳሰብና አመለካከት ለውጥ መምጣት ጀምሮ አበረታች ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

የሴቶች ግርዛት፣ ያለዕድሜ ጋብቻና ጠለፋ በማህበረሰቡ ውስጥ የነበሩ አደገኛ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መሆናቸውን  የጠቀሱት ሚኒስቴሯ  በተካሄዱ ህብረተሰብ አቀፍ ንቅናቄዎች ችግሩን 90 በመቶ መቀነስ መቻሉን አስረድተዋል።

" በኦሮሚያ፣ትግራይ፣አማራ፣ደቡብ፣አዲስ አበባና ድሬዳዋ ላይ ችግርቹን ከመከላከል አንፃር አመርቂ ውጤት ያስመዘገብንበት ነው" ብለዋል።

በአፋር፣ሶማሌ፣ቤንሻንጉልና ጋምቤላ ክልሎች የህብረተሰቡ አስተሳሰብና አመለካከት በግንዛቤ ደረጃ የተለወጠና ድርጊቱን በመከላከል መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም የሚፈለገው ውጤት እንዳልመጣ ተናግረዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለማስቀረት  ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት አጋዥ የሆነ ሀገራዊ ንቅናቄ ለማካሄድ የሚረዳ እቅድ ተዘጋጅቶ  ወደ ተግባር መግባቱን አስታወቀዋል፡፡

በመድረኩ ጥናታዊ ጽሁፍ በሚኒስቴሩ የሴቶች ተሳትፎና ንቅናቄ ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ታደሰ በበኩላቸው በሀገሪቱ በተደረጉ የስነ ህዝብ ዳሰሳ ጥናት ከ140 በላይ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሴቶችና ህፃናት ላይ እንደሚፈጸሙ ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች  የሴቶች ግርዛት፣ ያለዕድሜ ጋብቻ፣የጎሮሮ ማስቧጠጥና ጠለፋ በዋናነት የሚስተዋሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ናቸው፡፡ ።

" 60 በመቶ የሚሆነው የሴት ልጅ ግርዛት ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ ባሉት ህፃናት ላይ ይፈፀማል " ብለዋል።

ከህግ፣ፖሊስና ስትራቴጂ የመነጨ ህብረተሰብ አቀፍ ሀገራዊ ንቅናቄ በማካሄድ ችግሩን በአብዛኛው  መከላከል  መቻሉን አስረድተዋል።

በክልሉ ከሚስተዋሉት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መካከል  ያለእድሜ ጋብቻ እንዱ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ንቅናቄ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ስማቸው ዳኜ  ናቸው።

አምና ከ5ሺህ 600 በላይ የሚሆኑ ያለ እድሜ ጋብቻ እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን ጠቅሰው የሴቶች ግርዛትና ተያያዥ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ከ98 በመቶ በላይ መቀነስ እንደተቻለም አመልክተዋል።

"ውጤቱ ሊመጣ የቻለው የኃይማኖት አባቶች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣የሴቶች አደረጃቶችና የፍትህ አካላት የጋራ እቅድ በማውጣት ባደረጉት ርብርብ ነው "ብለዋል።

በመድረኩ ከሁሉም ክልሎችና የሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች  የተወጣጡ  የኃይማኖት አባቶች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣የሴቶች አደረጃቶችና የፍትህ አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም