የኢትዮጵያ የባህል ዲፕሎማሲ ቀን ጥር 4 ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህል ዲፕሎማሲ ቀን ጥር 4 ይከበራል
አዲስ አበባ ታህሳስ 24/2011 የኢትዮጵያ የባህል ዲፕሎማሲ ቀን በመጪው ሳምንት ጥር 4 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚከበር ተገለጸ።
በዓሉ የኢትዮጵያውያን ባህል፣ ቅርስና ታሪክ ለአፍሪካዊያን ዲፕሎማቶች ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ረዳኢ ግርማይ በበዓሉ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሃላፊዎችን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረትና የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ይገኛሉ ብለዋል።
በተጨማሪም ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆኑ የሃምሳ አምስቱ አፍሪካ አገሮች አምባሳደሮች፣ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ልዩ ልዩ አካላት እንደሚገኙም ተጠቅሷል።
በዕለቱ የእንጦጦ ቤተ-መንግስትና ሙዚየም፣ የአዲስ አበባ የቱሪስት መዳረሻዎች እና ያያ ቪሌጅ እንደሚጎበኙ ተናግረዋል።
የአገራችን ጥበባትና ባህላዊ እሴቶች፣ ባህላዊ ሙዚቃዎችና ባህላዊ ምግቦች እንዲሁም የከተማችን ቅርሶች፣ ለአፍሪካዊያን ወንድሞቻችን በስፋት የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራም አመልከተዋል።
መድረኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በጋራ የሚያዘጋጁት መሆኑን ዳይሬክተር ጄኔራሉ መግለጻቸውን ከቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።