በአዳማ 50 ሺህ ሀሰተኛ የብር ኖቶች ተያዘ

115

አዳማ ታህሳስ 24/2011 በአዳማ ከተማ ዛሬ 50 ሺህ ሐሰተኛ የብር ኖቶች መያዙን የአዳማ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ገለጸ።

የመምሪያው የህዝብ ግኑኝነት ዲቪዥን ከፍተኛ ባለሙያ ዋና ሳጂን ወርቅነሽ ገልሜቻ ለኢዜአ እንደገለጹት መጪውን የገና  በዓል አጋጣሚ በመጠቀም ሐሰተኛ ባለ መቶ የብር ኖቶች በብዛት ወደ ገበያ እንዲገቡ እየተደረገ  ነው።

በአዳማ ከተማ አባ ገዳ ክፍለ ከተማ ኦዳ ቀበሌ ልዩ ስሙ አሮጌ መናኽሪያ አካባቢ ዛሬ የተያዘው 50 ሺህ ሐሰተኛ ባለ መቶ የብር ኖቶች በግብይት ላይ እንዳለ መሆኑ የዚህ ማሳያ ነው፡፡

ሐሰተኛ የብር ኖቶችን የያዘው ግለሰብ  ጠዋት ሦስት ሰዓት ተኩል ላይ የተለያዩ አልባሳትን በተያዘው ሀሰተኛ የብር ኖት  ሳይከራከር እየመዘዘ ሲገዛ ሻጮች በጥርጣሬ ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ እንደተደረሰበት ዋና ሳጂን ወርቅነሽ አስታውቀዋል።

የገና በዓልን እንደ አጋጣሚ በመጠቀም  ለማጭበርበር  የተዘጋጁ ግለሰቦች መኖራቸውን ፖሊስ መረጃ የደረሰው በመሆኑ ህብረተሰቡ እራሱን ከተጋላጭነት በመጠበቅና የተለየ ክስተት ሲያጋጥመው ለፖሊስ በመጠቆም ወንጀሉን በጋራ እንዲከላከል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።

የንግዱ ማህበረሰብም በሸቀጥ ልውውጥ ወቅት የሚቀበለው ገንዘብ ጤናማ መሆኑን እንዲያረጋግጥ ዋና ሳጂን ወርቅነሽ አሳስቧል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም