" ይቅርታ ፍቱን የሰላም መሳሪያ "

አሸናፊ በድዬ (አምቦ ኢዜአ)

ጊዜው የመደመር፣ የይቅርታና የእርቅ ዘመን ነው፡፡ በመደመር ውስጥ ደግሞ ሰላም አለ፡፡ ሰላም ለሁሉም ነገር መሠረት ነው፡፡

ሰዎች ወጠተው ለመግባት ፣ ነግደው ለማትረፍ ፣ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ፣ መንግስትም የህዝቡን የመሠረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ ሰላም በእጅጉ ያስፈልጋል። ሰላም በሌለበት የህዝቦችን የተረጋጋ ሕይወትንና አንድነትን ማሰብ አይቻልም፡፡

ሀገር ማለት ሰው ነው ፡፡ ሰው ደግሞ ግለሠብ ፡፡ ግለሰብ ሠላም ከሆነ አካባቢ ሰላም ይሆናል ፡፡ የአካባቢ ሰላም መሆን ለክልል ሠላም መረጋገጥም ዋስትና ነው ፡፡

በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ሰዎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚጋጩበት አጋጣሚ ይፈጠራል።

ነገር ግን ሰው ማህበራዊ ኑሮውን እያካሄደ ባለበት ሂደት በትንሽ ነገር ተጋጭቶ እስከ ትልቁ ነፍስ ማጥፋት ድረስ የሚደረስበት ሁኔታም በርካታ ነው፡፡

እንደ እኛ ሀገር ላሉ ሁሉ ነገራችን በህብረት በሚከውነው ህብረተሰብ ውስጥ የእርስ በእርስ ግጭት መከሰቱ አይቀርም ፡፡ ለምሣሌ  የእርሻ ስራችንን ብንመለከት መሬቱን ከማረስ ጀምሮ እስከ ሰብል ስብሰባ ድረስ ያለው ሂደት በህብረትና በደቦ የሚሰራ ነው፡፡

በዚህ ጥሩ ባህል ስር  ሆነን እንኳን  አንዳንድ ጊዜ የእርስ በእርስ ግጭት ያጋጥማል ። ግጭቱ ወደ ጉዳት ሳይሸጋገር በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በምክክር መፍታት ቀዳሚ አማራጭ ነው።

ግጭቱ አፈትልኮ ወደ ጉዳት ከተሸጋገረ ደግሞ ፍቱኑ የሰላም መሳሪያ ይቅርታ ሆኖ እናገኘዋለን ።

በምዕራብ ሸዋ ዞን ኢሉ ገላን ወረዳ ለበርካታ ዓመታት በመካከላቸው በነበረው ደም መቃባት ምክንያት በጠላትነት ሲተያዩ የነበሩ ግለሰቦች ከጠላትነት ወደ እግር መተጣጠብ መሸጋገራቸውን ለዛሬው ጽሁፌ መነሻ አደረግኩት ።

የግለሰቦቹ የእርቅ ማውረድ ስነ ስርዓት በመካነ ኢየሱስ ቤተክርሰቲያን አማካኝነት የተፈጸመ ነው ። ቤተ እምነቶች ህዝቡን ስለ እምነታቸው አስተምህሮ ከማስተማር ባለፈ እንዲህ ዓይነት በጎ ምግባር በመፈፀምም ይታወቃሉ ።

አቶ ሚደጋ ነመራ በምዕራብ ሸዋ ዞን ኢጃጃ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡  በ2003 ዓመተ ምህረት ወንድማቸው አቶ ጪምዴሣ ነመራ አገር አማን ነው ብሎ ወደ ገበያ ቢወጣም ወደ ቤቱ ሳይመለስ ይቀራል ።

አቶ ጪምዴሣ ነመራ ያልተመለሱበት ምክንያት በመንገድ ላይ በተፈጠረ ድንገተኛ ጥል ህይወታቸው በማለፉ መሆኑም ታወቀ፡፡

በዚህ ጊዜም አቶ ሚደጋ የወንድማቸውን ደም ለማፈስ የገዳይ ቤተሰብ ፈልገው ለመበቀል ቢያሥቡም በጊዜው ህግ መሀከላቸው በመግባቱ ገዳይ ወደ ፍርድ ቤት ቀርቦ ውሳኔ አግኝቷል፡፡

ነገር ግን ገዳይ ወደ ማረሚያ ቤት ከወረደ በኋላም ቢሆን የገዳይ ቤተሰብ የሆኑትን እነ አቶ ተስፋዬ ተምትሜ ግን ሰላም አላገኙም ። ለ7 ዓመታት ያህል አንድም ቀን እንኳን ደህና እንቀልፍ ተኝተው እንደማያውቁ ይናገራሉ፡፡ 

" ሁል ጊዜ ውጪ አምሽተን መግባት አንችልም። ሌሊት ከውጪ ድምጽ በሰማን ቁጥር ለልጆቻችን እንሰጋ ነበር " ሲሉ አቶ ተምትሜ ይናገራሉ፡፡

ባላሰቡትና ባልገመቱት ሁኔታ ወንድማቸው በድንገተኛ አለመግባባት  የጎረቤታቸውን ሰው ነፍስ በማጥፈቱ ከማህበራዊ ህይወት ተነጥለው አሰቃቂ ህይወት ማሳለፋቸውን ሲናገሩ የሰሚውን  አንጀት ይበላሉ፡፡

የእነ አቶ ሚደጋ ነመራ ቤተሰቦችም ቢሆኑ የወንድማቸውን ደም ለመመለስ በማሰብ አንድም ቀን የሰላም እንቅልፍ ተኝተው እንደማያውቁ መስክረዋል፡፡

ከህብረሰተቡ የሚሰነዘርባቸው ቃላት ደግሞ ከሁሉ በላይ አንቅልፍ ይነሣቸው እንደነበር ምስክረነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

" የወንድምህን ደም ሳትመልስ እንዴት በህዝቡ ውስጥ ለመመላለስ ትደፍራለህ ። ደም ደግሞ በደም ነው  የሚመለስው እያሉ ብዙ ሰዎች ይናገሩኝ ነበር " ይላሉ - አቶ ሚደጋ፡፡

እኔ ወንድሜን ቀብሬ ወደ ቤቴ እንደገባሁ ጉዳዩን ለፈጣሪ ብቻ ሰጥቼ ለመተው ባስብም በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ ደግሞ ፈሪና የወንድሙን ደም ያልተበቀለ ሰው ተብዬ ስለምጠራ ለረጅም ጊዜ  ለበቀል ተነሳስተው እንዲዘልቁ እንዳደረጋቸው  አስረድተዋል፡፡

አሁን ግን የሃይማኖት አባቶች ቤቴ መጥተው ጉዳዩን ለፈጣሪ ሰጥቼ ይቅር እንድል  ሲለምኑኝ አምቢ ለማለት አልደፈርኩም ይላሉ አቶ ሚደጋ፡፡

ከዛም ለእርቅ ተቀምጠን በሰላማዊ ሁኔታ ተመራርቀን ታረቅን ። ጉዳዩን እዛው  ዘግተን ማህበራዊ ኑሮአችንን ሰላማዊ አደረግነው ይላሉ ፡፡   

ዘመኑ የእርቅና የአንድነት ነው እና ነገሩን በሰሙበት ጊዜ  ሰዎችን ማስታረቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን የገለፁት የኢጃጂ መካነ ኢየሱስ ቤተክርሰቲያን ቄስ ፈይሣ ቶሎሣ ናቸው ፡፡

በቤተክርስቲያኗ መተዳደሪያ ደንብ መጽሐፍ ገጽ 242 ላይ ደም ስለ ተቃቡ ሰዎች የእርቅ ሁኔታ /ሲርና አራራ ጉማ ሚርከኔሱ/ ይናገራልና በዚህ መሰረት ነው እርቅ ለማውረድ የቻልነው ሲሉም ያስረዳሉ ።

ቤተ-ክርስቲያኗ የህዝቦችን ሰላም መሆን ፣ መፋቃቀርና መዋደድ ለሀገሪቷ ልማትም ወሳኝ ሚና አለው ብላ ታምናለች ይላሉ ፡፡

ለ7 ዓመታት በጠላትነት ሲተያዩ የነበሩና ሊገዳደሉ የሚፈላለጉ እነ አቶ ሚደጋ እና እነ አቶ ተስፋዬን የእርቅ ስነ ስርዓት በሰላማዊ ሁኔታ ተፈጽሟል፡፡

የአጥፊው ወገን እነ አቶ ሚደጋ ለተበዳይ ለተለያዩ ወጪ ያወጡትን 11ሺህ 077 ብርና የካሣ 9 ሺህ 999 ብር እንዲከፍሉ ተደርጎ ተመራርቀው ተለያይተዋል፡፡

በጠላትነት መጠባበቁ ቀርቶም አንዱ ሌለኛው ቤት ገብቶ መዓድ ቀምሶ እግር ተጣጥበው በሰላም መለያየታቸውን ነግረውናል፡፡

ለመሆኑ ይህ ታሪክ እንደ መነሻ ወሰድን እንጂ ቤተክርሰቲያኗ በዚህ ዓመት ብቻ ከ18 አባወራ በላይ ተመሣሣይ ጉዳይ ያለባቸውን ሸምግላ አስታርቃ በሰላም እንዲኖሩ ማድረጓን ከቄስ ፈይሣ ቶሎሳ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

ቤተክርስትያኗ ያከናወነቸው መልካም ተግባር በአካባቢው መስተዳድር እውቅና የተሰጠው ሲሆን አርአያነቱን ሌሎች አጠናክረው እንዲቀጥሉበትም ጥሪ ቀርቧል ። ድርጊቱ የመደመር ትክክለኛው ማሳያ ተደርጎም ተወስዷል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም