በሀዋሳ ከተማ በማህበር ለተደራጁ 186 ወጣቶች የመስሪያ ቦታ ተሰጠ

97

ሀዋሳ ታህሳስ 24/2011በሀዋሳ ከተማ በ23 ማህበራት ለተደራጁ 186 ስራ አጥ ወጣቶች የመስሪያ ቦታ ዛሬ በዕጣ ተሰጣቸው፡፡

የመስሪያ ቦታ ከተሰጣቸው ስራ አጥ ወጣቶች መካከል 158ቱ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ተመርቀው ስራ ያላገኙ ወጣቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ የጎዳና ተዳዳሪዎች ናቸው፡፡

ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ የትምህርት መስክ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀው ወጣት አስቻለው ይስሀቅ እንዳለው ከተመረቀ በኋላ ስራ ፍለጋ ለወራት ተንከራቷል፡፡

''ቤተሰብ አስተምሮ እዚህ ካደረሰ በኋላ እንደገና ሸክም ሆኖ መቀመጥ ከባድ ነው'' የሚለው ወጣት አስቻለው በማህበር ተደራጅቶ በመስራት መለወጥ እንደሚቻል ከጓደኞቹ ማየት በመቻሉ ለመደራጀት መወሰኑን ገልጿል፡፡

ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ ዘጠኝ ጓደኞቹን በማስተባበር በምግብ ዝግጅት ስራ ለመሰማራት በማህበር ተደራጅተው ዛሬ ቦታ መቀበላቸውን ገልጿል፡፡

በሀዋሳ ከተማ መናኸሪያ አካባቢ በጎዳና ተዳዳሪነት ከሰባት ዓመት በላይ እንደቆየ የሚናገረው ወጣት አራምዳቸው ጴጥሮስ በበኩሉ በጎዳና ላይ ሲኖር በርካታ ችግሮችን እንደተጋፈጠ ገልጿል፡፡

ህብረተሰቡ ለጎዳና ተዳዳሪ የሚሰጠው አመለካከት ዝቅተኛ በመሆኑም ከባድ ጊዜ እንዳሳለፈና አሁን ግን የምስራቅ ክፍለ ከተማ በፈጠረለት እድል መሰረት 14 ሆነው በመደራጀት በመኪና እጥበት ስራ ለመሰማራት የመስሪያ ቦታ እንደተሰጣቸው ተናግሯል፡፡

በተሰማሩበት የስራ መስክ ራሳቸውን ለመለወጥና ለሌሎች አርአያ ለመሆን  ጠንክረው እንደሚሰሩ አስታውቋል፡፡

የምስራቅ ክፍለ ከተማ ነዋሪና የመስሪያ ቦታው በእጣ ሲተላለፍ ታዛቢ ሆነው የተገኙት አቶ ሀጎስ አዲሱ ቀደም ሲል በማህበር ተደራጅተው ቦታ የሚሰጠው በዘመድና በሌሎች መንገዶች እንደሆነ ሲነገር እንደነበርና አሁን ግን በእጣ መሰጠቱ ትክክለኛ መንገድ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የምስራቅ ክፍለ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ማቲዮስ ማናየ እንዳሉት በዚህ አመት በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች የሚተላለፍ ከ3 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ ቦታ ተዘጋጅቷል፡፡

የምስራቅ ክፍለ ከተማ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ሹዱራ በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ እንዳሉት ባለፉት አራት ወራት ውስጥ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ 929 ወጣቶችን ወደ ስራ ማስገባት ተችሏል፡፡

ክፍለ ከተማው ከዚህ ቀደም በማህበር የተደራጁና በውላቸው መሰረት አምስት አመት የሞላቸውን ማህበራት በራሳቸው አቅም የፈጠሩ በመሆኑ ቦታ አስለቅቆ ለሌሎች ለማስረከብ እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

ቦታ ላለመልቀቅ የሚደረገው ጥረት ከፍተኛ እንደሆነ የተናገሩት አስተዳዳሪው ከማህበራቱ ጋር ውይይት በማድረግ አንድ ሺህ 689 ካሬ ሜትር ቦታ በዛሬው እለት በማህበር ለተዳራጁ 186 ወጣቶች ማስተላለፍ እንደተቻለ ጠቁመዋል፡፡

ማህበራቱ ወደ ስራ እንዲገቡ ለማድረግ የመንቀሳቀሻ ብድር ከተዘዋዋሪ ፈንዱ 8 ሚሊዮን ብር እንደተዘጋጀ በዚሁ ጊዜ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም