ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ የምዕራብ ሸዋ ዞን አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ገለፁ - ኢዜአ አማርኛ
ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ የምዕራብ ሸዋ ዞን አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ገለፁ
አምቦ ታህሳስ 24/2011 ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡን በመምከርና በማስተማር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ በምዕራብ ሸዋ ዞን የሚገኙ አባ ገዳዎች ፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ገለፁ።
አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት በምዕራብ ኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ ጥረት እያረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢሉ ገላን ወረዳ የገዳ ሜጫ መሪ አባ ገዳ ከበደ ኢጀታ የገዳ ሥርዓት የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ህዝቦችን አቅፎ ማኖር የሚያስችል በመሆኑ በሰላም እሴት ግንባታ ሂደት ገንቢ ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል፡፡
አባገዳዎች በህዝቡ ዘንድ ያላቸውን ተደማጭነት በመጠቀም ወጣቱ የአካባቢውን ሰላም እንዲጠብቅ መስራት እንደሚገባ የጠቆሙት አባ ገዳ ከበደ የወጣቱን ተሳታፊነት በማጠናከር የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ለማሳካት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ህዝቡን አንድ በሚያደርጉና ሰላምን በሚያስጠብቁ አማራጮች ዙሪያ ተስማምተው መስራት እንዳለባቸውም አባገዳው አሳስበዋል፡፡
አባቦኩ መጫ አዱኛ ለታ በበኩላቸው የአካባቢው ህዝብ ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥና አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት ከመንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል ።
ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በሰላምና በህብረት እንዲኖሩ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አባቦኩ መጫ አዱኛ ገልጸዋል፡፡
ሰላምን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊጠብቀው እንደሚገባ የገለጹት አባበኩ መጫ አዱኛ ለታ ማንኛውም በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳሰቀስ የፖለቲካ ድርጅት ችግሮች ሲያጋጥሙት በኦሮሞ ባህል መሰረት ከአባ ገዳዎች ጋር በመሆን ችግሮችን ሊፈታ ይገባል፡፡
የፖለቲካ ድርጅቶች ችግሮችን የግጭት መነሻ በማድረግ ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት መሆን እንደሌለባቸው አመልክተዋል፡፡
የሀገር ሽማግሌ አቶ ደለሳ ቡርቃ ወጣቱ እንደ አገር የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ዳር ለማድረስ የበኩሉን እንዲወጣ የማስተማር ስራ በመስራት አባታዊ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል፡፡
እንደሀገር ሽማግሌነታቸው ህብረተሰቡ ለሰላም ዘብ እንዲቆም የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የሃይማኖት አባት የሆኑት መላከ ዓርያም ቀሲስ ዮሐንስ በየነ ሰላምን መጠበቅ ለመንግስት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ምዕመናን ለሰላም ልዩ ቦታ እንዲሰጡ የማስተማር ስራ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሼክ መሐመድ ገመቲ በበኩላቸው ህብረተሰቡ ሰላምን ከራሱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ነጥሎ ማየት እንደሌለበት ገልጸው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ምንም አይነት ፖለቲካዊ አመለካከት ቢኖረውም ፍላጎቱን ለማሟላት ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥ መክረዋል።