ቀጥታ፡

ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች ግጭት ተሳትፎ በነበራቸው አምስት ተማሪዎች ላይ የዲስፕሊን እርምጃ ወሰደ

ጎንደር ታህሳስ 24/2011 የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ተፈጥሮ በነበረው የተማሪዎች ግጭት ግንባር ቀደም ተሳትፎ በማድረግ ችግሩ እንዲባባስ አድርገዋል ባላቸው አምስት ተማሪዎች ላይ የዲስፕሊን እርምጃ መወሰዱን አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀጃው ደማሙ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት እርምጃ ከተወሰደባቸው ተማሪዎች መካከል ሁለቱ ከዩኒቨርሲቲው እንዲሰናበቱ ተደርጓል፡፡

ሌሎች ሁለት ተማሪዎች ደግሞ የአንድ አመት የትምህርት ክፍለ ጊዜ እንዳይከታተሉ ተወስኗል"

አንድ ተማሪ በከባድ ማስጠንቀቂያ ወደ ትምህርት ገበታው እንዲመለስ  መደረጉን ተናግረዋል ።

እንደ ፐሬዝዳንቱ ገለጻ የዲስፒሊን ውሳኔው የተወሰደው ለዩኒቨርሲቲው ሴኔት(የዩኒቨርስቲው የቦርድ አባላት) ቀርቦ ከፀደቀ በኋላ ነው ።

በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በዘንድሮ የትምህርት ዘመን 1ሺህ 600 አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችለውን የተማሪዎች የማደሪያ ህንጻ ግንባታ በማፋጠን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፈው አመት ተመርቆ ስራ የጀመረው ዩኒቨርሲቲው 1ሺህ የሚጠጉ የሁለተኛ አመት ነባር ተማሪዎችን በማስተማር ላይ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም