ሀገራዊ ለውጡን በክልሉ ለማስቀጠል አደረጃጀቱን ማጠናከር መጀመሩን ኢሶህዴፓ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ለውጡን በክልሉ ለማስቀጠል አደረጃጀቱን ማጠናከር መጀመሩን ኢሶህዴፓ አስታወቀ
ጅግጅጋ ታህሳስ 23/2011የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ዴሞክራሳዊ ፓርቲ/ ኢሶህዴፓ/ ሀገራዊና ክልላዊ የለውጥ ሂደቱን ለማስቀጠል የሚስያስችለውን ፖለቲካዊ ቁመና ላይ ለመገኘት የውስጥ አደረጃጀቱን ማጠናከር መጀመሩን አስታወቀ።
ፓርቲው ለመካከለኛው አመራር በሀገራዊ ለውጡ ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል ያዘጋጀው መድረክ በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ አህመድ ሽዴ መሀመድ በመድረኩ እንደገለጹት ፓርቲው በክልሉ ተከስቶ በነበረው ቀውስ ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት የመሩና የተሳተፉ አመራር አባላቱን በማስወገድ በአዲስ አመራር ተክቷል።
ከሁሉም በላይ በሀገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ሀገራዊ ገጽታ ይዞ እንዲጠናከር ለማድረግ የክልሉን መንግስት የሚመራው ኢሶህዴፓ ለከፍተኛና መካከለኛ አመራሩ እንዲሁም ለአባላቱ ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የለውጥ አመራሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆትና ተቀባይነት ያተረፈ ሀገራዊና አህጉራዊ እርምጃዎች መውሰዱን ጠቅሰዋል፡፡
"ከእነዚህ እርምጃዎች መካከል የትጥቅ ትግል ሲያካሄዱ የነበሩ ፓርቲዎች ሰላማዊ ትግል ውስጥ መግባታቸው ለሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት አስተዋጽኦ አለው "ብለዋል።
በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በውጪ ተቃዋሚ ኃይል የሌለበት ወቅት መደረሱን ያመለከቱት አቶ አህመድ ከጎረቤት ሀገራትም የጋራ ጥቅምና እድገት ፣ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር የለውጥ አመራሩ ውጤታማ ስራ ማከናወኑን አስረድተዋል፡፡
በኃይማኖቶች መካከል የነበረው መቃቃር እንዲፈቱ የበኩሉን ተወጥቷል።
አቶ አህመድ እንዳሉት ሀገራዊ የለውጥ አመራሩና ኢሶህዴፓ ከኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር ጋር የደረሰው የሰላም ስምምነት ሌላው ማሳያ ነው።
" ኦብነግ ለአባላቱ የተዘጋጅላቸው ካምፕ እንዲገቡ ከአመራሩ ጋር ተስማምተናል፤ በክልሉ መሳሪያ ይዞ መንቀሳቅስ አይቻልም፤ ኦብነግ ሰላማዊ ትግል እንዲያካሄድ ተፎካካሪ ድርጅት እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል " ብለዋል።
ከአንድ ሺህ ስድስት መቶ በላይ የኢሶህዴፓ መካከለኛ አመራር አባላት ለሶስት ቀናት በሚቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫው መድረክ እየተሳተፉ ነው፡፡