ቀጥታ፡

የጤናው ዘርፍ ተደራሽ መሆኑ የተለያየ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት አስችሎናል - ሆስፒታሎች

አዲስ አባበ ግንቦት 17/2010 የህክምና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የተሰራው ስራ የተለያዩ የህክምና አይነቶችን ለመስጠት እንዳስቻላቸው በአዲስ አበባ የሚገኙ ሆስፒታሎች ገለጹ። ኢትዮጵያ ስኬታማ ለውጦችን ካስመዘገበችባቸው መስኮች መካከል የጤናው ዘርፍ ተጠቃሽ ነው። በዚህም የአገልግሎቱን ተደራሽነት በሚመለከት ኢዜአ በቅዱስ ጳውሎስ፣ በየካቲት አስራሁለትና በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታሎች ቅኝት አድርጓል። ሆስፒታሎቹ የህክምና አገልግሎታቸውን ተደራሽ ለማድረግ በሚያደርጉት ማስፋፊያ የተለያዩ ህክምናዎችን መስጠት እንዳስቻላቸው ነው የሚገልጹት። በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የህክምና ዘርፍ ምክትል ፕሮቮስት ዶክተር ብርሃኔ ረዳኢ እንዳሉት፤ ሆስፒታሉ ለረጅም አመታት በነበረበት የአቅም ውስንነት የተነሳ የውስጥ ደዌ፤ የማህጸንና ጽንስ ህክምናን ብቻ ይሰጥ እንደነበር አስታውሰዋል። አዲሱ ሚሌኒየም ከገባ ወዲህ ሆስፒታሉ ተደራሽነቱን ለማስፋት የተለያዩ ማስፋፊያዎችን በማከናወኑ የማስተማሪያ ኮሌጅ አቋቁሞ የተለያየ የህክምና አገልግሎት ለመጀመር እድል እንደፈጠረለትና የህክምና አገልግሎት ለሚሹ ዜጎች ተደራሽ እንደሆነ አክለዋል። ለረጅም ዓመታት በቲቢና በሳምባ በሽታዎች ተወስኖ የህክምና አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአሁኑ ወቅት የአገልግሎት አድማሱን በማስፋትና የሰው ኃይል ቁጥሩን በመጨመር በርካታ አገልገሎቶችን መስጠት ጀምሯል። የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ያዕቆብ ሰማን እንደገለጹት፤ ሆስፒታሉ በአዲስ መልክ ከተደራጀ በኋላ በተለይም ከ2004 ዓ ም ጀምሮ የማስፋፊያ ህንጻዎችን ገንብቶ ያጠናቀቀ በመሆኑ የተለያዩ የህክምና አይነቶችን በመስጠት አገልግሎቱን ተደራሽ አድርጓል ብለዋል። የልብ ህክምና፣ የማህጸንና ጽንስ፣ የህጻናትና የጨቅላ ህጻናት ህክምና፣ የቆዳ ህክምና፣ የህጻናት የስነ አእምሮ ህክምና፣ የድንገተኛና የመመረዝ ህክምና በአሁኑ ወቅት በሆስፒታሉ ከሚሰጡ የህክምና አይነቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው። ሆስፒታሉ በቀን ከ10 በላይ ከፍተኛ የቀዶ ህክምናና ከ20 በላይ እናቶችን የማዋለድ ዓቅም ላይ መድረሱን ጠቁመዋል። የየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅም የማስፋፊያ ስራዎች በማከናወኑ የሚሰጣቸውን የህክምና አይነቶች አሳድጓል። በሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስትና ዋና ስራ አስኪያጅ ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል አበበ እንደሚሉት፤ ሆስፒታሉ በተደረገለት የማስፋፊያ ስራ የተገነባው ህንጻ ተጨማሪ የህክምና አገልግሎትን ለመጀመር አስችሏል። በአሁኑ ወቅት የህክምና ትምህርት መስጠት የጀመረው ሆስፒታሉ ከዚህ ቀደም የአስተኝቶ ህክምና ይሰጥ የነበረው በ168 አልጋ ብቻ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 356 ተጨማሪ አልጋዎች ተሟልተውለት አገልግሎት እየሰጠ ነው። ለተለያዩ ህክምናዎች ወደ ሌሎች ሆስፒታሎች ይደረግ የነበረውን ህሙማንን ወደሌላ ሆስፒታል የመላክ አሰራር ማስቀረቱን ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ የህክምና መሳሪያና የመድሃኒት አቅርቦት ከፍላጎቱ ጋር ያልተመጣጠነ በመሆኑ አገልግሎት አሰጣጡ እንዲስተጓጎል አድርጓል። ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ411 ሆስፒታሎች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አስታውቋል። በዚሁ መሰረት አገሪቷ የጤና ፖሊሲዋ ላይ ተመሰርታ ''ጤናን በሁሉም ዘንድ ማዳረስ'' የሚል እቅድ ቀርጻ እየሰራች መሆኗ የጤና አገልገሎት ተደራሽነት ማሳያ ነው ብሏል። በተለይም የጤና ፖሊሲው ተግባራዊ በተደረገበት 25 ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የላቀ ውጤት እያስመዘገበች እንደሆነ ገልጿል። ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን እንደገለጹት፤ የጤና ፖሊሲው ከወጣ ጀምሮ ኢትዮጵያ የምእተ ዓመቱን ግቦችን በማሳካት በተለይም ጤናን ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሚያደርጉ ፕሮግራሞችን በመቀየስ ትልቅ ውጤት አስመዝግባለች። የጤና መሰረተ ልማትን ተዳራሽ በማድረግ ውጤታማ ስራ የሰራች ሲሆን ከ16ሺህ በላይ የጤና ኬላዎችና ከ3 ሺህ700 በላይ ጤና ጣቢያዎች የተገነቡ ሲሆን አንድ ጤና ጣቢያ ለ25 ሺህ ተደራሽ እንዲሆን መደረጉን ጠቁመዋል። ይህ መሆኑ ደግሞ በተለይም የእናቶችን ሞት በሁለት ሶስተኛ በመቀነስ፣ የህጻናትን ሞት በመቀነስ፣ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችና የቅድመ መከላከል ስራዎች ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገበችበት ተግባራት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል። በተጨማሪም ዋና ዋና ተብለው በጥናት የተለዩትን ጉዳዮች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራቱም እንዲሁ በአለም አቀፍ ደረጃ የምእተ አመት ግቡን ለማሳካት የተቀመጠውን አቅጣጫ ከተገበሩ አገሮች አንዷ እንድትሆን አስችሏታል። ይሁን እንጂ አሁንም የተሟላና የህብረተሰቡን ፍላጎት በማሟላት  የጤና አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ረገድ ክፍተቶች እንዳሉ ሚኒስትሩ አንስተዋል። የጤና አገልግሎቱ ጥራቱን የጠበቀ እንዳይሆን ካደረጉት መካከል ብቁ የህክምና ባለሙያ አለማፍራት፣ ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎች በበቂ ሁኔታ አለመሟላትና የመድሃኒት አቅርቦቱ ከፍላጎቱ ጋር ተመጣጣኝ አለመሆን አሁንም ያልተፈቱ ችግሮች ናቸው። ሌላው ፍትሃዊ የሆነ የጤና አገልግሎት ተደራሽ አለመሆን በተለይም የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በቂ የህክምና ማእከላት አለመኖርና የህክምና ባለሙያው “ሩህሩህ፣ ተንከባካቢና አገልጋይ'' የሚለውን መርህ በሚፈለገው ደረጃ አለመተግበር እንዲሁ በጤና አገልግሎቱ ላይ እንቅፋት እንደሆነ ተናግረዋል። ችግሩን ለመቅረፍና የሁለተኛውን ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ጥራት፣ ፍትሃዊነት፣ የመረጃ ተደራሽነትና የህክምና ባለሙያዎች ስነምግባር በትኩረት እንዲሰራባቸው የተለዩ መሆናቸውን ተናግረዋል። በተለይም የጤናውን ዘርፍ ይበልጥ ለማሻሻል ከወረዳ ጀምሮ በጥራት እንዲሰራ ለማድረግ ‘ወረዳ ትራንስፎርሜሽን’ የተባለ አሰራርር ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም