በኮንስትራክሽን ዘርፍ የምርታማነት ልኬት ፕሮጀክት የሙከራ ትግበራ ሊጀመር ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኮንስትራክሽን ዘርፍ የምርታማነት ልኬት ፕሮጀክት የሙከራ ትግበራ ሊጀመር ነው
አዲስ አበባ ታህሳስ23/2011 የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር "በምርታማነት ልኬት" ፕሮጀክት ሙከራ ትግበራ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ጠየቀ።
የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስትትዩት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር የህንጻ ግንባታ ፕሮጀክቶች "በምርታማነት ልኬት ፕሮጀክት" ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ካሊድ አብዱርሃማን እንደገለጹት የኮንስትራክሽን ዘርፉን የሃብት ብክነትና የግንባታ መጓተት ያስቀራል ተብሎ የታመነበት የምርታማነት ልኬት ፕሮጀክት የሙከራ ትግበራ ዝግጅት ተጠናቋል።
የምርታማነት ልኬት ፕሮጀክት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን የግንባታ ሂደት መከታተል የሚያስችል መሆኑን የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታው ግንባታ ከመጀመሩም በፊት የሚፈለገውን የሰው ሃይል፣ የግብዓትና የብር መጠን ለማወቅ ያስችላል ብለዋል።
በመሆኑም ከስራው ጠባይ አዲስነትና በአገር አቀፍ ደረጃ ወደ ሥራ ለመግባት ፕሮጀክቱ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ የሙከራ ትግበራ ለመጀመር ዝግጅ መደረጉን ተናግረዋል።
በሙከራ ትግበራው ወቅት የሚገኙ ግብዓቶችን በመቀመር ለሃገራዊ የምርታማነት ልኬት ትግበራ እንዲውል የባለድርሻ አካላት ፣ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ተቋማትና የህዝብ ክንፍ ተሳትፎና ትብብር አስፈላጊ ነው።
በመሆኑም ለሙከራ ትግበራው የምርታማነት ሙከራ የሚደረግባቸው የተመረጡ ተቋማት፣ የፕሮጀክት ባለቤቶች፣ ስራ ተቋራጮች፣አማካሪዎችና ተቆጣጣሪዎች ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አርጋው አሻ በበኩላቸው የፕሮጀክቱ ትግበራ መጀመር ለግንባታው ዘርፍ ውጤታማነት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ የሰው ሃይልና የግብአት አቅርቦትን ለመወሰን ከማገዙም በተጨማሪ ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜና የገንዘብ በጀት እንዲጠናቀቁ ያግዛል ብለዋል።
በምርታማነት ልኬት ከተወዳደሩ 79 የዓለም አገሮች ኢትዮጵያ 77ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ያሉት ዳይሬክተሩ የፕሮጀክቱ መጀመር በብዙ መልኩ መሻሻል እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህርና የፕሮጀክቱ ኃላፊ ዶክተር አብርሃም አሰፋ እንደሚሉት የኮንስትራክሽን ዘርፉ በየዓመቱ ከ60 በመቶ በላይ የካፒታል በጀት የሚመደብለት ቢሆንም ተወዳዳሪነቱ ግን ዝቅተኛ ነው።
በአገሪቷ ከሚካሄዱ ግንባታዎች 88 በመቶው የምርታማነት ልኬት (efficiency measurement) የማይደረግላቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ይህም የማይሆነው በቸልተኝነት፣ በግንዛቤ እጥረትና በተለይም የምርታማነት ልኬት እውቀት ማነስ መሆኑንም አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ በህንጻ ግንባታ የሚጀመረው ፕሮጀክት እየተጠናከረ ሲሄድ ከሁለት ዓመት በኋላ በውሃና በመንገድ ግንባታ ዘርፍም ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በአፋጣኝ ወደ ተግባር ቢገባ በህንጻ ግንባታ ዘርፍ የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታት ያግዛል ብለዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ኢንጂነር ከበደ አበበ እንደሚሉት እስካሁን ከዩንቨርስቲዎች ጋር የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ውጤታማ ስላልሆኑ በቀጣይ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል።
ኢንጂነር ዘላለም ካራ የተባሉት አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው ፕሮጀክቱን በአገር አቀፍ ደረጃ ለመተግበር በአስተማማኝ መረጃ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የምርታማነት ልኬት ዝግጅት ከ20 ዓመት በፊት የወጣ ሲሆን አገሪቱና አለም ከደረሰበት የግንባታው ዘርፍ ጋር የተጣጣመ የምርታማነት ልኬት ሥራ ለመስራት ፕሮጀክቱ ተዘጋጅቷል።